ሰለሞን ሀብቴ ወደ ምዓም አናብስት ለመመለስ ተስማማ

መቐለ 70 እንደርታ የቀድሞው ተጫዋቹን ለማስፈረም ሲስማማ የነባር ተጫዋቾች ውል አራዝሟል።

ቀደም ብለው የቦና ዓሊን ዝውውር ያገባደዱት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ የግራ መስመር ተከላካዩ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል። ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ደግሞ በ2013 ቡድኑን ለመቀላቀል ፊርማውን አኑሮ በጦርነቱ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ያልቀጠለው ሰለሞን ሀብቴ ነው።

በግራ መስመር ተከላካይነት እና አማካይ ቦታ ላይ መጫወት የሚችለው ሁለገቡ ተጫዋች በ2008 አሳዳጊ ክለቡ ደደቢትን ለቆ ወደ ወላይታ ድቻ ካመራ ከአንድ ዓመት በኋላ በድጋሚ ወደ ክለቡ ተመልሶ ሁለት የውድድር ዘመናት በደደቢት፤ በመቀጠል ደግሞ በፋሲል ከነማና ሲዳማ ቡና ከተጫወተ በኋላ ባለፈው የውድድር ዓመት አርባምንጭ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካሳደገ ስብስብ አንድ አካል ነበር።  በነገው ዕለት በይፋ ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎ የሚጠበቀው ተጫዋቹ  በደደቢት ታዳጊ ቡድን ካሰለጠነው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬን ጋር በድጋሜ የሚገናኝ ይሆናል።

በተያያዘ ዜና ክለቡ የአምስት ተጫዋቾች ውል ለማደስ መስማማቱ በፌስቡክ ገፁ ይፋ አድርጓል። በቡድኑ ለተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት የተስማሙ ተጫዋቾች ደግሞ ከሁለተኛ ቡድኑ አድገው ባለፈው የውድድር ዓመት በዋናው ቡድን ደረጃ ያገለገሉት አማኑኤል ልዑል፣ ዘርእሰናይ ብርሀኑና ግደይ ሕሉፍ እና ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞ የኢትዮጵያ መድን፣ ስሑል ሽረ፣ ወላይታ ድቻ እንዲሁም በሁለት አጋጣሚዎች ቡድኑን ያገለገለው ተከላካዩ ዮናስ ግርማይ፤ የቡድኑ አምበልና የግራ መስመር ተከላካዩ አንተነህ ገብረክርስቶስ፤ አማካዩ ኬኔዲ ገብረፃድቅ እና ባለፈው የውድድር ዓመት የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ክብሮም አፅብሀ  ናቸው።