ስሑል ሽረ ሦስት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማምቷል

ስሑል ሽረዎች ሦስት ተጫዋቾች ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ተስማምተዋል።

ቀደም ብለው ጋናዊው ተከላካይ ሱሌይማን መሐመድና ዩጋንዳዊው አጥቂ አሌክስ ኪታታን ለማፈረም የተስማሙት ስሑል ሽረዎች አሁን ደግሞ የሦስት ተጫዋቾች ፌርማ ለማግኘት ከስምምነት ደርሰዋል። ክለቡን ለመቀላቀል የተስማሙት ተጫዋቾች ደግሞ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ፋሲል አስማማው እና ብርሀኑ አዳሙ ናቸው። ባለፈው የውድድር ዓመት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታ የነበረው የቀድሞ የሰበታ ከተማ ፣ ባህር ዳር ከተማና ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ በውድድር ዓመቱ በስድስት ጨዋታዎች ተሰልፎ 540 ደቂቃዎች ቡድኑን አገልግሏል።

ሁለተኛው ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ደግሞ ባለፈው የውድድር ዓመት ከሸገር ከተማ ጋር ድንቅ ዓመት ያሳለፈውና በዓመቱ አስራ ሰባት ግቦች ያስቆጠረው የቀድሞ ለገጣፎ ለገዳዲ ፣ ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ አጥቂ ፋሲል አስማማው ነው። ሌላኛው ወደ ቡድኑ ለማቅናት ከስምምነት የደረሰው የቀድሞ የአርባምንጭ ፣ ሀምበሪቾ በተጠናቀቀው ዓመት ባቱ ከተማ የመስመር ተጫዋች ብርሀኑ አዳሙ ሆኗል።