ሲዳማ ቡና ዝግጅት የሚጀምርበት ወቅት ታውቋል

በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመሩት እና በክረምቱ ወሳኝ ዝውውሮችን የፈፀሙት ሲዳማ ቡናዎች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሊጀምሩ ነው።

የተጠናቀቀውን የ2016 የውድድር ዘመን በጥቅሉ በሦስት አሰልጣኞች የተመራው እና በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ዓመቱን የቋጨው ሲዳማ ቡና 11ኛ ደረጃን በ40 ነጥቦች ይዞ ካጠናቀቀበት ያለፈው ዓመት ተሳትፎው በተሻለ ቁመና ላይ ሆኖ ለመገኘት ለቀጣዩ የ2017 የውድድር ዘመን ወሳኝ ዝውውሮችን በመፈፀም ከነገ ጀምሮ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት እንደሚገባ ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።

ክለቡ በዝውውሩ ከፕሪምየር ሊጉ ክለቦች መፍን ታፈሰ ፣ አበባየሁ ሀጂሶ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ፍራኦል መንግስቱ ፣ ያሬድ ባዬ ፣ ሬድዋን ናስር እና ሀብታሙ ታደሠን ከከፍተኛ ሊጉ ደግሞ ወጣቱን ኤርምያስ ደጀኔ በዩጋንዳ ሊግ ዓመቱን በስኬት ያጠናቀቀውን ግብ ጠባቂው ቶም ኢካራን በአዲስ መልክ የቡድናቸው አካል ያደረጉ ሲሆን የጋናዊውን አጥቂ ማይክል ኪፕሮቪን ውልም ማራዘማቸው ከሰሞኑ ይታወሳል። ነባር አዲሶቹን ተጫዋቾች በመያዝ የክለቡ አጠቃላይ የቡድን አባላት በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ታደሠ እንጆሪ ሆቴል ከተሰባሰቡ በኋላ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ነገ ማክሰኞ ሐምሌ 30/2016 በይፋ ይጀምራሉ።