በአሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ የሚመሩት ኢትዮጵያ መድኖች የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቁ ነባሮችን ውል አራዝመዋል።
በተጠናቀቀው ዓመት ሁለት የውድድር መልክን በመያዝ ዓመቱን የፈፀሙት ኢትዮጵያ መድኖች ከቀናቶች በፊት ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ዳዊት ተፈራን አዲሱ ፈራሚያቸው ያደረጉ ሲሆን የግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ የአጥቂውን መስፍን ዋሼ ኮንትራት ደግሞ ማራዘማቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ ክለቡ ሁለት አዲስ ተጫዋችን ሲጨምር የሦስት ነባር ተጫዋችን ውል ደግሞ አድሷል።
ዮሐንስ ሶጌቦ ወደ ሊጉ ተመልሷል። በአማካይ እና በግራ መስመር ተጫዋችነት ከሀዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን የተገኘው ተጫዋቹ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሀዋሳ ቆይታ ወቅት ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ያገለገለ ሲሆን ከቆይታ በኋላ ደግሞ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አምርቶም የመጫወት አጋጣሚ የነበረው ሲሆን መድንን ለማገልገል ለአንድ ዓመት መቀላቀሉ ታውቋል።
ሌላኛው ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች የመስመር አጥቂው ያሬድ መሐመድ ነው። ከሀዋሳ ወጣት ቡድኖች የተገኘው እና በደደቢት ፣ ነገሌ አርሲ እና አምና ደግሞ በጅማ አባቡና ያሳለፈው ይህ ወጣት ተጫዋች ወደ ቀደመ ክለቡ መድን ተመልሷል።
ሌላኛው ውሉን ያራዘመው ሀቢብ ከማል ነው። በኢትዮ ኤሌክትሪክ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ሀቢብ በኮልፌ ፣ በአርባምንጭ ከተማ ካሳለፈ በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በመድን ቤት ቆይታ ካደረገ በኋላ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በቡድኑ የሚቆይበትን ውል አራዝሟል።
በተጨማሪም ከክለቡ ወጣት ቡድን የተገኙትን የተከላካዩ ዋንጫ ቱት እና የአማካዩ ዳዊት አውላቸውን ውልም አድሰዋል።