መቐለ 70 እንደርታ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጀምሯል

በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ የሚመሩት ምዓም አናብስት ልምምድ ጀምረዋል።

በአስከፊው ጦርነት ምክንያት ላለፉት ዓመታት ከሀገር አቀፍ ጨዋታዎች ርቀው የቆዩት የ2011 ቻምፕዮኖቹ መቐለ 70 እንደርታዎች ከዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ በዝግጅት ላይ ናቸው። ቡድኑ ላለፉት ሁለት ቀናት ውል ያራዘሙትን ነባር ተጫዋቾቻቸውን በሞሞና ሆቴል በማሰባሰብ ለቅድመ ውድድር ዝግጅቱ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ከቆየ በኋላ በትናንትናው ዕለት ልምምድ ጀምሯል። በጂምናዝየም የጀመረው የቡድኑ ዝግጅት በቀጣይ ቀናት በሜዳ የሚቀጥል ይሆናል።

በተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ድጋፍ ዳግም ወደ ውድድር ከተመለሰ በኋላ ባለፈው የውድድር ዓመት በትግራይ እግርኳስ ፌደሬሽን አዘጋጅነት በተካሄደው ውድድር የዋንጫ ባለቤት የሆነው ክለቡ ከዚህ ቀደም በስሑል ሽረ እና ደደቢት እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንና መቻል ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ ያገለገለውን ዳንኤል ፀሐዬ በዋና አሰልጣኝነት ቀጥሮ አስር አዳዲስ ተጫዋቾች በማስፈረም የነባር ተጫዋቾች ውል ማራዘሙ ይታወሳል።