ኢትዮጵያ ቡና የተጫዋቾች የዝውውር ህግ ጥሰዋል ባላቸው ክለቦች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ እንዲራዘምለት ጠይቋል።
ኢትዮጵያ ቡና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያፀደቀው የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያን በማስታወስ አንዳንድ ክለቦች መመሪያውን ጥሰው በአንድ የውድድር ሜዳ ላይ ተፎካካሪ ሆኖ ለመሳተፍ አስቸጋሪ እንደሆነ የገለፀበትን ደብዳቤ ለሁለቱ አካላት ልኳል።
‘የፀደቀውን መመሪያ በማክበራችን ምክንያት በቡድን ግንባታው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጥሮብናል’ ያለው ክለቡ በዋናው ቡድን ከነበሩት ቋሚ ተጫዋቾች መካከል ብዙዎቹ ውል እንዲያድሱ ድርድር እያደረገ ሳለ ክለቡ ካቀረበላቸው ደመወዝ ባነሰ የደመወዝ ክፍያ ለሌሎች ክለቦች መፈረማቸውን ጠቅሶ ‘መመሪያውን ለማክበር የሄድኩበት ረጅም መንገድ ክለቡን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ፌዴሬሽኑ መመሪያውን በጣሱ ክለቦች ላይ አስቸኳይ የዕርምት እርምጃ ይውሰድልኝ’ ሲል ጠይቋል።
ክለቡ ጨምሮ እንዳለውም ሁኔታው ተጫዋች ለማስፈረም እና ለውድድር ዝግጅት ከፍተኛ መሰናክል ስለሆነበት ነሀሴ 5 የሚደረገውን የአሸናፊዎች አሸናፉ ፍጻሜ ጨዋታ ለማከናወን እንደሚቸገር እና ከኬኒያ ፖሊስ ጋር ነሀሴ 12 ከሚያደርገው ጨዋታ ጋር መቀራረቡም የዕረፍት እና የጉዞ ጊዜን የሚያጣብብ በመሆኑ በውጤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ፌዴሬሽኑ እንዲረዳው ጠይቋል።
በዚህም መሰረት ክለቡ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ ሌሎች ክለቦች ፈፅመውታል ባለው የህግ ጥሰት ላይ በመመሪያው መሰረት እርምጃ እንዲወሰድ እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነሀሴ 5 እንዲደረግ የታቀደው የአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ መርሃ ግብር ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘምለት ጠይቋል።