መቻል ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው መቻል የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከቀናት በኋላ ይጀምራል።

የተጠናቀቀውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን የሊጉን ክብር ለማሳካት ከጫፍ ደርሶ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተነጠቀው መቻል ለቀጣዩ የውድድር ዘመን በይበልጥ ተጠናክሮ ለመቅረብ በክረምቱ የዝውውር ገበያ አማኑኤል ዮሐንስ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ እና አለምብርሀን ይግዛውን ከፕሪምየር ሊግ ዳንኤል ዳርጌ እና ፊልሞን ገብረፃዲቅን ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ቡድኑ ያመጣ ሲሆን የከነዓን ማርክነህ ፣ በረከት ደስታ ፣ ደሳለኝ ከተማ ፣ ምንይሉ ወንድሙ ፣ ዳዊት ማሞ እና ነስረዲን ሐይሉ ደግሞ ውላቸው ተጠናቆ ስለነበር በክለቡ ተራዝሞላቸዋል።

የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት ያራዘመው ቡድኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅትን መቼ እንደማጀምሩ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ በደረሳት መረጃ አውቃለች። የፊታችን ዕሁድ የቡድኑ አባላት ከተሰባሰቡ በኋላ በማግስቱ ሰኞ ነሐሴ 6/2016 ቢሾፍቱ በሚገኘው ዐየር ሐይል ሜዳ ላይ ልምምዳቸውን በይፋ ይጀምራሉ።