መቐለ 70 እንደርታ የቀድሞው ተጫዋቹን እና
በትግራይ ዋንጫ የደመቀውን የመስመር አጥቂ ለማስፈረም ተስማምቷል።
የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬው መቐለ 70 እንደርታ ቡድኑን ለማጠናከር አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርሞ የበርከት ያሉ ነባር ተጫዋቾች ውል ማራዘሙ ይታወቃል። ቡድኑ ከዓመታት በኋላ ለሚመለስበት ሊግ ራሱን ለማጠናከር ተጨማሪ ሁለት ተጫዋች ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል ተስማምቷል። ወደ ክለቡ ለመቀላቀል የተስማሙት ተጫዋቾች ደግሞ በ2012 ከክለቡ ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳው አማካዩ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና ከስሑል ሽረ ጋር ያሳለፈው የመስመር ተጫዋቹ ናትናኤል ተኽለ ናቸው።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ መጫወት የቻለው ሙሉጌታ የመጀመርያውን ዙር ባሳለፈበት ኢትዮጵያ ቡና የመሰለፍ ዕድል ባያገኝም በሁለተኛው ዙር በተቀላቀለበት ሻሸመኔ ከተማ ግን በዘጠኝ ጨዋታዎች (593 ደቂቃዎች) ቡድኑን አገልግሏል። ከዚህ በፊት በሁለት አጋጣሚዎች እናት ክለቡ መቐለን ማገልገል የቻለውና በመቻል ፣ ወልድያ ፣ ወልቂጤ ከተማ ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ሻሸመኔ ከተማ መጫወት የቻለው አማካዩ ከዓመታት በኋላ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ለመመለስ ከስምምነት ደርሶ ቡድኑ ወደ አረፈበት ሆቴል ተቀላቅሏል። በቀጣይ ቀናትም በይፋ የክለቡ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለተኛው ቡድኑን ለመቀላቀል ከጫፍ የደረሰው ተጫዋች ደግሞ ባለፉት ዓመታት በስሑል ሽረ ቆይታ የነበረው ናትናኤል ተኽለ ነው። ከስሑል ሽረ ታዳጊ ቡድን የተገኘውና በ2011 ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ያለፉት ዓመታት አሳዳጊ ክለቡን በማገልገል የቆየው ይህ ተጫዋች የትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባዘጋጀው ውድድር ላይ ስምንት ግቦች በማስቆጠር ጥሩ የውድድር ዓመት ካሳለፈ በኋላ መቐለ 70 እንደርታን ለመቀላቀል ከስምምንት ደርሷል። ከመቐለ 70 እንደርታ ተወካዮች ካደረገው ድርድር በኋላ የህክምና ምርመራው በተሳካ ሁኔታ ያገባደደው ተጫዋቹ መቐለን ለመቀላቀል መስማማቱን ተከትሎ ወደ ታዳጊ ቡድና እና ዋናው ቡድን ካሳደገው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ጋር በድጋሜ ይገናኛል።
ከመቐለ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ላለፉት ቀናት በጄምናዝየም የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረው ክለቡ በቀጣይ ቀናት የሜዳ ላይ ዝግጅቱን እንደሚጀምር ታውቋል።