በ2013 አጋማሽ ወር ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጋር የተዋወቀው ፈጣኑ ተጫዋች ወደ ግብፅ ሊግ አምርቷል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ተስፋ ሰጪ ከሆኑ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል የሀድያ ሆሳዕናው የመስመር አጥቂ ተመስገን ብርሀኑ ይጠቀሳል። ሆሳዕና ከተማ ላይ ካለ ፕሮጀክት መነሻውን ካደረገ በኋላ 2012 ላይ የሀድያ ሆሳዕናን ከ20 ዓመት በታች ቡድን የተቀላቀለው ፈጣኑ ተጫዋች በ2013 የውድድር ዘመን እስከ ዓመቱ አጋማሽ ለሀድያ ሆሳዕና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ጥሩ አቅሙን እያሳየ በነበረበት ወቅት የዋናው ቡድን ተጫዋቾች ከክፍያ ጋር በተያያዘ አንጫወቱም ባሉበት ወቅት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በዓመቱ አጋማሽ ወራት ላይ ከታች መጥቶ ቡድኑን እንዲያገለግል ካደረጉት በኋላ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ለአሳዳጊ ክለቡ በፕሪምየር ሊጉ ግልጋሎት እየሰጠ እስከ ተጠናቀቀው ዓመት ድረስ ቆይታን ማድረግ ችሏል።
ውሉ ባሳለፍነው ሰኔ ወር መጨረሻ የተቋጨው ይህ ወጣት ተጫዋች የግብፁን ክለብ በይፋ መቀላቀሉን የተጫዋቹ ወኪል አዛሪያስ ተስፋፂሆን ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል። በግብፅ ፕሪምየር ሊግ በተጠናቀቀው ዓመት አልሀሊ ሻምፒዮን በሆነበት ወቅት በ52 ነጥቦች 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀቀው በ50 ዓመቱ አሰልጣኝ አሊ ማሂር የሚመራው እና ከተመሠረተ 104 ዓመታትን ያስቆጠረው አል – መስሪ አዲሱ የተመስገን ብርሀኑ ክለብም ሆኗል።