ድሬደዋ ከተማዎች ወደ ዝውውሩ በመግባት ሦስት ተጫዋቾችን ለማስፈረም መስማማታቸው ታውቋል።
ለቀጣይ የውድድር ዓመት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን የሾሙት ቡርትካናማዎቹ ከተለያዩ ውል ካላቸው ተጫዋቾች ጋር በስምምነት እየተለያዩ ቢሆንም አሁን ደግሞ ሦስት ተጫዋቾችን ለማስፈረም መቃረባቸውን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል። ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማሙት አህመድ ረሺድ፣ አስራት ቱንጆ እና አቡበከር ሻሚል ናቸው።
ከደደቢት ከተገኘ በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ባህርዳር ከተማ፣ በመቻል እና አዳማ ከተማ ቆይታ የነበረው የመስመር ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ አህመድ ከዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ቀድሞ ክለቡ በመመለስ ድሬደዋ ከተማ ለመጫወት መስማማቱ ታውቋል።
የቀኝ መስመር ተከላካይ አስራት ቱንጆ ከጅማ አባ ጅፋር ከተጫወተ በኋላ ያለፉትን ስድስት ተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ሲጫወት ቆይቶ አሁን መዳረሻው ወደ ምስራቁ ተወካይ ድሬደዋ ከተማ ለመሆን እንደተስማማ አውቀናል።
አማካዩ አቡበከር ሻሚል በኮልፌ ቀራንዮ ፣ በአርባምንጭ ከተማ እና በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በአዳማ ከተማ ሲጫወት ቆይቶ ለድሬደዋ ከተማ ለመጫወት ከተስማሙት ተጫዋቾች መካከል ሦስተኛው ለመሆን ተቃርቧል።
ሦስቱም ተጫዋቾች የህክምና ምርመራ ያደረጉ ሲሆን በቀጣዮ ጊዜያት ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።