ስሑል ሽረዎች ተከላካዩን ለማስፈረም ተስማሙ

ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ከብርቱካናማዎቹ ጋር ቆይታ የነበረው ተጫዋች ወደ ስሑል ሽረ ለማምራት ተስማማ።

ስድስት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማምተው የአስራ ሦስት ነባር ተጫዋቾችን ውል ያራዘሙት ስሑል ሽረዎች በዝውውር መስኮቱ ሰባተኛ ተጫዋቻቸውን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል። ክለቡን ለመቀላቀል የተስማማው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ነው። ያለፉትን ሁለት ዓመታት በድሬዳዋ ከተማ ቆይታ የነበረው ይህ ተጫዋች ባለፈው የውድድር ዓመት በአስራ ሰባት ጨዋታዎች ተሳትፎ 1518′ ደቂቃዎች ብርቱካናማዎቹን ሲያገለግል አሁን ደግሞ ከቡድኑ ጋር ያለውን ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ስሑል ሽረ ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል።

ከዚህ ቀደም በክለብ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሀያ ሦስት ዓመት በታች መጫወት የቻለው ተከላካዩ የህክምና ምርመራውን በተሳካ ሁኔታ ማገባደዱን ተከትሎ በቀጣይ ቀናት በይፋ ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል።


ከስሑል ሽረ ጋር በተያያዘ መረጃ ክለቡ ቀደም ብሎ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በመቐለ ከተማ እንደሚያደርግ በይፋዊ ገፁ ቢያሳውቅም አሁን ባገኘነው መረጃ ዝግጅቱን በሽረ እንዳስላሴ ከተማ ለማድረግ እንደወሰነ ለማወቅ ተችሏል።