ነብሮቹ በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዝግጅታቸውን ይጀምራሉ

የአሰልጣኝ ግርማ ታደሠው ሀድያ ሆሳዕና በክለቡ መቀመጫ ከተማ ልምምድ የሚጀምሩበት ዕለት ታውቋል።

ያለፈውን የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጀምረው በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ዓመቱን ባጠናቀቁት ግርማ ታደሠ መሪነት በ41 ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የቋጩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በቀጣዩ ዓመት ለሚኖራቸው የፕሪምየር ሊግ ውድድር ቀደም በማለት የአሰልጣኝ ግርማ ታደሠን ውል ለአንድ ዓመት በማራዘም በመቀጠልም ደግሞ የቃለአብ ውብሸት ፣ ከድር ኩሊባሊ ፣ መለሠ ሚሻሞ እና ሳሙኤል ዮሐንሰን ውል ካደሱ በኋላ እዮብ አለማየሁ ፣ በረከት ወንድሙ ፣ ጫላ ተሺታን ብሩክ በየነን በማስፈረም ስብሰባቸው ሲያጠናክሩ ቆይተው ወደ ዝግጅት ሊገቡ መሆኑን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል።

የፊታችን ዕሁድ የቡድኑ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች በሆሳዕና ከተማ በሚገኘው የክለቡ ካምፕ ከተሰባሰቡ በኋላ በማግስቱ ሰኞ ነሐሴ 6/2016 በይፋ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በአቢዩ ኤርሳሞ ስታዲየም ማከናወን ይጀምራሉ።