የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሊጀምር ነው።
ከአንድ ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመለሱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ቀደም ብለው ከዚ ቀደም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለተከታታይ ሁለት ዓመታት የሊጉ ዋንጫ ያሳካው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን በዋና አሰልጣኝነት ከቀጠሩ በኋላ ለቀጣይ የውድድር ዘመን ተጠናክረው ለመቅረብ የተለያዩ ስራዎችን ከውነዋል።
ክለቡ አሸብር ተስፋዬ፣ ገለታ ኃይሉ፣ ዲንግ ኪያር፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ፣ ሄኖክ ገብረህይወት እና አብዱላዚዝ አማን ከከፍተኛ ሊግ ያመጣ ሲሆን ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ፣ ሽመክት ጉጉሳ፣ ፍቃዱ አለሙ፣ ሐብታሙ ሸዋለምን ደግሞ ከፕሪሚየር ሊጉ አስፈርሟል። የስድስት የቡድኑ ነባር ተጫዋቾችም ውል አራዝሟል።
አሁን ደግሞ ቡድኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅትን መቼ እንደማጀምሩ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ በደረሳት መረጃ አውቃለች። ነገ ጠዋት የቡድኑ አባላት ከተሰባሰቡ በኋላ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ በማድረግ ከሰዓት ጎፋ በሚገኘው የክለቡ የልምምድ ሜዳ ዝግጅቱን የሚጀምር ይሆናል።