ኮማንደሩ የዳንኤል ፀሐዬን የአሰልጣኞች ቡድን ተቀላቀለ

መቐለ 70 እንደርታዎች ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኝ ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል።


በክረምቱ ዝውውር መስኮት ንቁ ተሳትፎ ካደረጉ ክለቦች መካከል የሚጠቀሱት መቐለ 70 እንደርታዎች ቡድኑን የማጠናከር ስራቸው አጠናክረው በመቀጠል ተጨማሪ የአሰልጣኞች ቡድን አባል አካተዋል። የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ምክትል ሆኖ ቡድኑን የተቀላቀለው ደግሞ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሲሳይ (ኮማንደር) ነው። ለረዥም ዓመታት በተጫዋችነት ባገለገለበት የትግራይ አንጋፋው ክለብ ዋልታ ፖሊስ ትግራይ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ቡድኑን ለዓመታት ማሰልጠን የቻለው አሰልጣኙ በ2002 እና 2003 በትራንስ ኢትዮጵያ በዋናና በረዳት አሰልጣኝነት የሰራ ሲሆን ከዛ በመቀጠልም ወደ ዋልታ ፖሊስ ትግራይ ተመልሶ እስከ ተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ድረስ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ሲመራ ቆይቷል።

ከክለብ እግር ኳስ በተጨማሪ የትግራይ ታዳጊ ቡድኖች ይዞ በሀገራዊ ውድድሮች በመሳተፍ የሚታወቀው ኮማንደር ዮሐንስ ሲሳይ በ1995 በአዳማ ከተማ፣ በ1999 በመቐለ ከተማ፣ በ2001 ደግሞ በዝዋይ በተዘጋጁ ሦስት ውድድሮች የክልሉ ታዳጊ ቡድን ይዞ ሻምፕዮን ሲሆን በ2000 ደግሞ የሴቶች ቡድን ይዞ የታዳጊዎች ውድድሩን አሸናፊ ሆኗል። አሁን ደግሞ በተጫዋችነትና በአሰልጣኝነት ለአስራ ስምንት ዓመታት ካገለገለበት አንጋፋው ዋልታ ፖሊስ ትግራይ ተለያይቶ ወደ መቐለ 70 እንደርታ አቅንቷል።