የአቡበከር ናስር ቀጣይ ማረፍያ?

የብራዚላውያኑ አሰልጣኝ ማንቆባ ምንኪቲ ስለ አቡበከር ናስር ቆይታ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ካከናወነበት ከአስቸጋሪው የውድድር ዓመት መልስ በኋላ በኦስትሪያ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን አጠናቆ አዲሱን የውድድር ዓመት መጀመር እየተጠባበቀ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው አጥቂ አቡበከር ናስር በክለቡ ስላለው ቆይታ፤ ተሰናባቹ አሰልጣኝ ሮላኒ ማክዌና ከወራት በፊት ከሰጡት አወዛጋቢ ቃለ-መጠይቅ ጀምሮ ብዙ ጭምጭምታዎች ተሰምተዋል። አሁን ደግሞ አዲሱ አሰልጣኝ ማንቆባ ምንኪቲ በተጫዋቹ ቆይታ ዙርያ ሀሳባቸው ገልፀዋል።

ሬድዩ 2000 በተባለ የሀገሪቱ ብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ በሚተላለፍ ‘Game on’ በተሰኘ ‘ፕሮግራም’ ባደረጉት ቆይታ ላይ ክለባቸው ከአዲሱ የውድድር ዘመን ጅማሮ በፊት አቡበከር ናስርን በውሰት ለመስጠት ማሰቡን ማረጋገጫ የሰጡት አሰልጣኙ ተጫዋቹ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ዝርዝር ውጪ ሆኖ መቆየቱ አስታውሰው አሁን ግን በጥሩ ሁኔታ እያገገመ እንዳለ ተናግረዋል። “ጥሩ እያገገመ ነው። አንዳንድ በጎ ምልክቶች እያሳየ ነው፤ ነገር ግን አሁንም ትንሽ ይቀረዋል። ተጫዋቹ አቅም ስላለው በጣም እንወደዋለን ነገር ግን ምናልባት እርግጠኛ ካልሆንን የያዘው የውጭ ተጫዋቾች ኮታ ተፈላጊ ስለሆነ የቋሚነት ዕድል ሊያገኝ በሚችልበት ቦታ የውሰት አማራጮች ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው” ብለዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም “ሙሉ በሙሉ አገግሟል ነገር ግን አንድ ዓመት ሙሉ አልተጫወተም እና ምናልባት የሆነ ቦታ በመደበኛነት መጫወት ከቻለ እስከ ታኅሣሥ ድረስ ልንመልሰው እንችላለን” ሲሉ አስረድተዋል።


ከውጤታማው አሰልጣኝ ሮላኒ ማክዌና መልቀቅ በኋላ ከባድ ኃላፊነት የተረከቡት የቀድሞ የጎልደን አሮውስ አሰልጣኝ አቡበከር ናስር ካሰለጠናቸው ምርጥ ተጨዋቾች አንዱ እንደሆነ በመጥቀስ መደበኛ የጨዋታ ጊዜ እንዲያገኝ በውሰት ማምራት እንዳለበት አስረግጠው ተናግረዋል። በ2022 ክለቡን ከተቀላቀለ ወዲህ በርካታ ጉዳቶች ያስተናገደው አጥቂው በሁሉም ውድድሮች 17 ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ጎሎች ማስቆጠሩ ይታወሳል።