ወልዋሎዎች ሦስት ተጫዋቾች አስፈርመዋል

ቢጫዎቹ ሦስት ተጫዋቾች ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።


ቀደም ብለው የቀድሞ ተጫዋቻቸው በረከት አማረን ጨምሮ አምስት ተጫዋቾች ወደ ቡድናቸው ለመቀላቀል የተስማሙት በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ የሦስት ተጫዋቾች ዝውውር አገባደዋል። ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማሙት ተጫዋቾች ደግሞ ታዬ ጋሻው፣ ኪሩቤል ወንድሙ እና ሰለሞን ገመቹ ናቸው።


ከአዳማ ከተማ ሁለተኛ ቡድን ከተገኘ በኋላ ለአንድ የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊጉ አርሴ ነገሌ መጫወት የቻለው ታዬ ጋሻው ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ወደ አሳዳጊ ክለቡ አዳማ ከተማ ተመልሶ ከተጫወተ በኋላ ማረፍያው ወልዋሎ ሆኗል። ከመሃል ተከላካዩ በተጨማሪ ክለቡን የተቀላቀሉት ደግሞ ባለፉት የውድድር ዓመታት ከንግድ ባንክ ጋር ቆይታ የነበረው የቀድሞ የለገጣፎ ለገዳዲ የግራ መስመር ተከላካይ ኪሩቤል ወንድሙ እና ባለፈው የውድድር ዓመት በአርሲ ነገሌ ቆይታ የነበረው እና የከፍተኛ ሊጉ የዓመቱ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ የተካተተው አማካዩ ሰለሞን ገመቹ ናቸው።