ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ጨምሯል

የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለው ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አግኝቷል።

በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ለቀጣዩ የውድድር ዘመን በቡድኑ የነበሩ ነባር ተጫዋቾች ከክለቡ በስምምነት እየተለያዩ የሚገኙ ሲሆን እነርሱን ለመተካት ደግሞ አዳዲስ ተጫዋቾችን ክለቡ ማስፈረም ጀምሯል። ቡድኑ አስራት ቶንጆ ፣ አህመድ ረሺድ ፣ መሐመድኑር ናስር ፣ አብዱሰላም የሱፍ ፣ አቡበከር ሻሚል እና መስዑድ መሐመድን በማስፈረም እና የያሬድ ታደሠ ፣ ሔኖክ ሐሰን እና አብዩ ካሳዬን ውል ያራዘመ ሲሆን ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን በማስፈረም የአዳዲሶቹን ቁጥር ስምንት አድርሷል።

ግብ ጠባቂው አላዛር መርኔ የምስራቁን ክለብ ተቀላቅሏል። የሀዋሳ ከተማ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖችን ጨምሮ በዋናው ቡድን ውስጥ አገልግሎ ከቆየ በኋላ በመቀጠል በኢኮስኮ ፣ ገላን ከተማ ፣ አርባምንጭ ከተማ እንዲሁም ደግሞ ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይቶ ቀጣዩ መዳረሻው ድሬዳዋ ሆኗል።

ሌላኛው ፈራሚ ተከላካዩ ድልአዲስ ገብሬ ነው። በመቻል እና አዲስ አበባ ከተማ ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች ውስጥ ተጫውቶ በመቀጠል ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና እንዲሁም ባለፈው የውድድር ዘመን ከደብረብርሃን ከተማ ጋር ያሳለፈው ወጣቱ ተጫዋች ቀጣዩ ክለቡ የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ድሬዳዋ ሆኗል።