ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ተስማምቷል

ጋናዊው ግብ ጠባቂ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለማምራት ተቃርቧል።

በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ቡድናቸውን ያጠናከሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ተስማምተዋል።
ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል ከጫፍ የደረሰው ተጫዋች ደግሞ ጋናዊው ግብ ጠባቂ አብዱላሂ ኢድሪሱ ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ከታንዛንያው አዛም ጋር በመሆን በካፍ በኮፌዴሬሽን ካፕ ባህር ዳርን ለመግጠም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሲጫወት የተመለከትነው ሲሆን ዘንድሮ ኸርትስ ኦፍ ኦክ ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው ይህ ግብ ጠባቂ ከጋናው ክለብ የነበረው የቃል ስምምነት ወደ ጎን አድርጎ ማረፍያው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለማድረግ ከስምምነት ደርሷል።

በ2021/22 የውድድር ዓመት የቤኬም ዩናይትድ ቆይታው ካከናወናቸው 31 ጨዋታዎች በ18 መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት የሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሽልማት ያሸነፈው ይህ ጋናዊ ወደ ኤሌክትሪክ የሚያደርገው ዝውውር በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።