የሴካፋ ዞን የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ቅደመ ዝግጅት አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል

“ውድድሩ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን ያገኛል ፤ መግቢያም በነጻ ነው።”

“የ600ሺህ ዶላር ድጋፍ የተጠየቀው ካፍ የ219ሺህ ዶላር ድጋፍ አድርጓል።”

“ፌዴሬሽኑ ለውድድሩ በትንሹ 30 ሚሊዮን ብር ያወጣል።”

“ውድድሩ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል”

ዛሬ 9 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ የአወዳዳሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሸረፋ ደለቾ እና የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ተገኝተው መግለጫውን ሲሰጡ ይህንን ውድድር ለማዘጋጀት በርካታ መሠረታዊ ነገሮች እንዳሉ ከእነዛም መካከል የሴቶች እግርኳስ በሀገራችን ደረጃ ላቅ ያለ ደረጃ (ቦታ) እና ውጤት ስላለውም ሆነ ለሴቶች እግርኳስ ልማት ያግዘናል ብለው እንደሚያስቡ ገልጸው በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ወደ ሀገራችን ለማምጣት እንቅስቃሴ በመጀመሩ ልምድ ለማካበት እና ዋናውን ጉዞ ለመጀመር እንዲሁም ሀገራችንን በመወከል የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከዛሬ ለዋንጫ እየደረሰ ሳይሳካለት መቅረቱ ለዚህም ደግሞ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ምክንያቶች እንዳሉ እና ውጫዊው ምክንያት የሜዳ አድቫንቴጅ ስለሚሆን እሱን ለማስተካከል መታሰቡ ሲሰማ “እግርኳሳችን ለዲፕሎማሲያችን” በሚል መርሕ ስፖርተኞችን ወደ አንድነት ፣ ወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች ወስዶ በማሳየት ቱሪዝምን በማጠናከር መልካም ስም መገንባት እንደሚቻል ተመላክቷል።

የታንዛኒያው ሲምባ 48 የቡድን አባላት እንዲሁም የተለያዩ ቡድኖች እስከ 35 የሚደርሱ የቡድን አባላትን ይዘው እስከዛሬ ድረስ ተጠናቀው እንደሚገቡ የተረጋገጠ ቢሆንም ካፍ ለእያንዳንዱ ቡድን እስከ 25 ለሚደርሱ የቡድን አባላት ብቻ ወጪ የሚችል ይሆናል።

የሜዳ ዝግጅት በተመለከተ ሴካፋ ሁለቱም ስታዲየሞች (አዲስ አበባ ስታዲየም እና አበበ ቢቂላ ስታዲየም ) ላይ ውድድሩ እንዲደረግ ቢፈልግም በቀን ሁለት ጨዋታ ስለሚደረግ እና ወቅቱ የዝናብ እንደመሆኑ ምርጫቸውን አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ማድረጋቸው ሲጠቆም ተሳታፊ ክለቦች በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሠሩ ሦስት አርቴፊሻል ሜዳዎች ማለትም ቤለር (አቧሬ አካባቢ) – ልደታ አካባቢ እና ሣር ቤት በሚገኙ አርቴፊሻል ተርፍ የተነጠፈባቸው ሜዳዎች ልምምድ እንዲሠሩ ተወስኗል።

ውድድሩ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን የሚሰጠው ሲሆን ተመልካቾች በነጻ ወደ ስታዲየም መግባት እንዲችሉ ተፈቅዷል።

አራት ኢትዮጵያዊን ዳኞች ማለትም ሁለት ዋና ዳኞች እና ሁለት ረዳት ዳኞች ውድድሩን ለመምራት በካፍ አማካኝነት ከኢትዮጵያ መመረጣቸው ሲነገር የውድድሩ ፕሮግራም ሊቀየር የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችልም ተጠቁሟል።

600ሺህ ዶላር ጠይቄ 219ሺህ ዶላር ብቻ ከካፍ ድጋፍ ተደርጎልኛል ያለው ፌዴሬሽኑ ለውድድሩ በትንሹ እስከ 30 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ ሲገልጽ ፌዴሬሽኑ 80ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ በመሆኑ እና በክለቦች ታሪክ የመጀመሪያውን የሴካፋ ውድድር እንደማስተናገዱ በደማቅ ሁኔታ ለማዘጋጀት መታቀዱ ተሰምቷል።

“እንግዳ ተቀባይነታችን መብታችንን እስኪገፉን ድረስ መሆን የለበትም” ያለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ዳኞች በካፍ ደረጃም ቢሆን በሀቀኝነታቸው እንደማይታሙ ጠቁሞ በሌሎች ነገሮች ግን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አበክሮ በመግለጽ የንግድ ባንክ ውጤታማነት ለፌዴሬሽኑ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ገልጿል።