ስሑል ሽረ የቀድሞ ተጫዋቹን ለማስፈረም ተስማማ

ጋናዊው ስሑል ሽረ ለመቀላቀል የተስማማ አስራ አንደኛው ተጫዋች ለመሆን ተቃርቧል።

ቀደም ብለው ሱሌይማን መሐመድ፣ አሌክስ ኪታታ፣ ፋሲል ገብረሚካኤል፣ ፋሲል አስማማው፣ ብርሀኑ አዳሙ፣ ኤልያስ አሕመድ፣ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ፣ ሙሉዓለም መስፍን፣ አዲስ ግርማ እና ነፃነት ገብረመድኅን ያስፈረሙት ስሑል ሽረዎች አሁን ደግሞ ከዚህ ቀደም በቡድኑ ቆይታ የነበረው ጋናዊው መሐመድ ዓብዱለጢፍ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ቆይታ የነበረው ይህ የግራ መስመር ተከላካይ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሀያ ሰባት ጨዋታዎች ተሰልፎ 2408′ ደቂቃዎች ቡድኑን ማገልገሉ ይታወሳል። ከዚ ቀደም በስሑል ሽረ ውጤታማ የስድስት ወራት ቆይታ የነበረው ይህ ጋናዊ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ሲዳማ ቡና፣ ስሑል ሽረ እና ድሬዳዋ ከተማ ከዛ በፊትም ለጋና ብሄራዊ ቡድን ጨምሮ ለፉትሮ ኪንግስና አሻንቲ ጎልድ መጫወቱ ሲታወስ አሁን ደግሞ ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ለመመለስ ከስምምነት ደርሷል።