የቻርለስ ሉክዋጎ ማረፍያ ታውቋል

ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ አዲስ ክለብ ተቀላቀለ።


ባለፈው የውድድር ዓመት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያሳለፈው እና ከዚህ ቀደም በሌላኛው የኢትዮጵያ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታ የነበረው ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ቻርለስ ሉክዋጎ በደቡብ አፍሪካው ሁለተኛ የሊግ እርከን ተሳታፊ ወደ ሆነው ክለብ ቬንዳ አምርቷል። ባለፈው የውድድር ዓመት በአስራ አምስት ጨዋታዎች ተሰልፎ 1305′ ደቂቃዎች ቡድኑን ማገልገል የቻለው ይህ ግብ ጠባቂ ከሀዋሳ ከተማ በመለያየት የሦስት ዓመት የኢትዮጵያ ቆይታውን አገባዶ ወደ ደቡብ አፍሪካው ክለብ አምርቷል።

የእግር ኳስ ሕይወቱ ፕሮላይን በተባለ የሀገሩ ክለብ ጀምሮ ለቪክቶርያ ዩኒቨርሲቲ፣ ልዌዛ እና KCCA መጫወት የቻለው ይህ ተጫዋች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሁለት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን ማንሳቱ ይታወሳል።