የንግድ ባንክ ሦስቱ ተጫዋቾች መቼ የዋልያዎቹን ስብስብ ይቀላቀላሉ ?

ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገላቸው ሦስቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች መቼ ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ታውቋል።

በቀጣዮቹ ቀናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለባት ወሳኝ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ትናንት ዝግጅቷን በይፋ መጀመሯ ይታወቃል ፤ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል የንግድ ባንኮቹ ግብጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ፣ ሱሌይማን ሀሚድ እና ፈቱዲን ጀማል ክለባቸው በነበረው የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑን ሳይቀላቀሉ ቀርተዋል።

እሁድ አመሻሽ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት ሦስቱ ተጫዋቾች ከዛሬ ጀምሮ ብሔራዊ ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ትናንት ባደረስናቹ መረጃ ገልፀን እንደነበር አይዘነጋም ፤ ሆኖም አሁን ባገኘነው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጪው ቅዳሜ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለሚኖረው ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ዝግጅት ሲባል ሦስቱ ተጫዋቾች ከቡድናቸው ጋር አብረው እንደሚቆዩ እርግጥ ሆኗል።

ሦስቱም ተጫዋቾች የመልሱን ጨዋታ ቅዳሜ ከተጫወቱ በኋላ በማግስቱ እሁድ ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ሶከር ኢትዮጵያ ተገንዝባለች።