አዳማ ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን ለማግኘት ተስማምቷል

በባቱ (ዝዋይ) የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ከጀመሩ አራት ቀናትን ያስቆጠሩት አዳማ ከተማዎች ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው አካተዋል።

ለ2017 የውድድር ዘመን አሰልጣኝ አብዲ ቡሊን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው አዳማ ከተማ የበለጠ ተጠናክሮ ለመቅረብ ያለፉትን ቀናት ሲያደርግ የነበረውን ጥረት በማጠናቀቅ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በባቱ (ዝዋይ) የጀመሩ ሲሆን ስንታየሁ መንግሥቱ፣ አቡበከር ወንድሙ እና አሜ መሐመድን ለማስፈረም መስማማታቸውን አውቀናል።

አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ በወላይታ ድቻ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ጅማሮ በወልቂጤ ከተማ ቆይታ አድርጎ የውድድር ዓመቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ በሻሸመኔ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን ዘንድሮ በሊጉ በአጠቃላይ ስድስት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

የመስመር አጥቂው አቡበከር ወንድሙ በሀላባ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በአዳማ ከተማ ቆይታ ካደረገ በኋላ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ለአንድ ዓመት ቆይቶ አሁን ለአዳማ ከተማ ለመጫወት ተስማምቷል።

ሌላው ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች አሜ መሐመድ ነው። የቀድሞው የጅማ አባ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወልቂጤ ከተማ ፣ አዳማ ከተማ እና የወልቂጤ ከተማ ተጫዋች በወልቂጤ ዘንድሮ አስከ አጋማሹ ከተጫወተ በኋላ ወደ ምስራቁ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ በማምራት መጫወቱ ይታወሳል።

አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ሌሎች ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ለማምጣት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።