ትውልደ ኢትዮጵያዊው በ”ሴሪ ሲ” ለሚሳተፈው ክለብ ፊርማውን አኑሯል

ሁለገቡ ተጫዋች አዲስ ክለብ ሲቀላቀል ሌላው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሴሪ ኤ የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ የጨዋታ ዕለት ስብስብ ውስጥ መካተት ችሏል።

ላለፉት ዓመታት በቶሪኖ የወጣት ቡድኖች ውስጥ ቆይታ የነበረው የአስራ ዘጠኝ ዓመቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊው አማካይ አሸናፊ ጃሬ በሴሪ ሲ ለሚሳተፈው ፕሮ ቬርሴሊ ፌርማውን አኑሯል።

በ2005 የተወለደው እና በቶሪኖ የወጣት ቡድን የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው ይህ በአማካይነት እንዲሁም በአጥቂ መስመር ላይ መጫወት የሚችለው ተጫዋች ባለፉት ዓመታት በቶሪኖ ከአስራ ሰባት፣ አስራ ስምንት እና አስራ ዘጠኝ ዓመት በታች ቡድኖች ከተጫወተ በኋላ ባለፈው የውድድር ዘመን በአለሳንድርያ ከአስራ ዘጠኝ ዓመት ቡድን የውሰት ቆይታን አድርጓል።

በአለሳንድርያ የአንድ ዓመት የውሰት ቆይታው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን በማሳየት በሀያ አምስት ጨዋታዎች ተሰልፎ አራት ግቦች በማስቆጠር አንድ
ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ከዚ ቀደም ከአስራ ሰባት ዓመት በታች የጣሊያን ብሄራዊ ቡድን መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ከአሳዳጊ ክለቡ ጋር ተለያይቶ በፋብዬ ካናቫሮ ታናሽ ወንድም ፓብሎ ካናቫሮ ወደ ሚሰለጥነው ፕሮ ቬርሴሊ ለማቅናት ፌርማውን አኑሯል።

በቶሪኖ ወጣት ቡድን ከነበሩ ሦስት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንዱ የሆነው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሀብታሙ ጋስቲም በሴሪ ዲ ለሚሳተፈው ሳርኔሴ የተባለ ክለብ በአንድ ዓመት የውሰት ውል አቅንቷል።

ቀደም ብለን ያስተዋወቅናቹ ሌላው የቶሪኖ አካዳሚ ውጤት የሆነውና ከወዲሁ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሮን ሲማግሊቼላ ከአስራ ዘጠኝ ዓመት የአውሮፓ ዋንጫ መልስ ቡድኑን ተቀላቅሎ ክለቡ ቶሪኖ ከኤሲሚላን ጋር አቻ በተለያየበት የሴሪ ኤ የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ የዋናው ቡድን አካል በመሆን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ አሳልፏል።