አቡበከር ናስር ብሔራዊ ቡድኑን መቼ ይቀላቀላል ?

የማሜሎዲ ሰንዳውንሱ አቡበከር ናስር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብን መቼ ይቀላቀላል?

በሞሮኮ አስተናጋጅነት በ2025 ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ብሔራዊ ቡድናችን የመጀመርያ ጨዋታውን ከታንዛንያ እና ከኮንጎ ዲ.ሪ ጋር ዳሬ ሰላም ብሔራዊ ስታዲየም ለሚያደርጋቸው ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ዝግጅቱን በወንጂ ስታዲየም እያደረገ ይገኛል።

ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ለደቡብ አፍሪካው ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እየተጫወተ የሚገኘው አቡበከር ናስር እስካሁን ብሔራዊ ቡድኑን ካልተቀላቀሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።

አቡበከር መቼ ብሔራዊ ቡድኑን ይቀላቀላል የሚለውን ጉዳይ ለማጣራት ባደረግነው ጥረት እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ አቡበከር ብሔራዊ ቡድኑ በሚቀላቀልበት መንገድ ዙርያ ከፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ጋር የስልክ ልውውጥ እንዳደረገ እንደሚገኝ እና አሁን ላይ ከክለቡ ጋር ዝግጅት ላይ የሚገኘው ተጫዋቹ በፊፋ ደንብ መሰረት ጨዋታው አንድ ሳምንት ወይም አምስት ቀን ሲቀረው ቡድኑን እንደሚቀላቀል ለማረጋገጥ ችለናል።