ከፍተኛ ሊግ | ደሴ ከተማ ወደ ዝውውሩ ገብቷል

ቀደም ብለው የዋና አሰልጣኛቸውን ውል ያራዘሙት ደሴ ከተማዎች የነባሮችን ውል በማደስ አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርመዋል።


በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ደሴ ከተማዎች በቀጣይ የውድድር ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ቀደም ብለው የዋና አሰልጣኝ ዳዊት ታደለን ውል ማራዘማቸው ይታወቃል፤ አሁን ደግሞ የነባር ተጫዋቾች ውል በማደስ እና አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ስብስባቸው በማካተት ወደ ዝውውሩ ገብተዋል።

በቡድኑ ለመቆየት ውላቸውን ያራዘሙት ባለፈው የውድድር ዓመት ከቡድኑ ጋር ጥሩ ጊዜ ያሳለፉት ወንድማማቾቹ አቡሽ ደርቤ እና ፀጋ ደርቤ ናቸው። ቡድኑን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾች ደግሞ ባለፈው የውድድር ዓመት በሀምበርቾ ቆይታ የነበረው የመሃል ተከላካዩ ትዕግስቱ አበራ፣ ዓመቱን ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር ያሳለፈው ግብ ጠባቂው ይስሃቅ ተገኝ፣ እንዲሁም ላለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በከፍተኛ ሊግ እና በፕሪምየር ሊጉ ሻሸመኔ ከተማን ያገለገለው ተከላካዩ ወጋየሁ ቡርቃ፣ በኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖች ጨምሮ ባቱ ከተማ፣ ገላን ከተማ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳደግ የሚታወቀው አማካዩ ጌታሰጠኝ ሸዋ እና ኢትዮጵያ መድን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቶ የወቅቱ የከፍተኛ ሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሽልማት የወሰደው ጆርጅ ደስታ በቀጣይ የውድድር ዓመት በክለቡ ለመጫወት ፊርማቸውን ያኖሩ ተጫዋቾች ናቸው።