ከዋልያዎቹ ስብስብ ሦስት ተጫዋቾች ወጥተው አንድ ተጫዋች ተጨምሯል

ሦስት ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጪ መሆናቸው ሲረጋገጥ ለአንድ ተጫዋች ጥሪ ተደርጓል።

ከታንዛኒያ እና ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ነሐሴ 29 እና ጳጉሜ 4 ቀን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ዳሬ ሰላም ላይ ጨዋታውን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅቱን ከጀመረ ዘጠነኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

ዋልያዎቹ ወደ ስፍራው ከማቅናታቸው አስቀድሞ እሁድ ዕለት በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ከኢትዮጵያ መድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርገው 1ለ0 ማሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ነሐሴ 27 ቀን ወደ ዳሬ ሰላም የሚያቀናው ስብስብ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎበታል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቻምፒየንነት ጉዞ ወሳኝ ሚና የነበረው የመስመር አጥቂው አዲስ ግደይ ጥሪ የተደረገለት ሲሆን የማሜሎዲ ሰንዳውንሱ አቡበከር ናስር ፣ የሲዳማ ቡናው መስፍን ታፈሰ እና ለግብጹ ዜድ ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው አቤል ያለው ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ መሆናቸው ተረጋግጧል።