የፋሲል ከነማ ተጫዋች ከቀናት በኋላ ወደ ሌጎስ ያቀናል።
ፋሲል ከነማ ከቀናት በፊት ከናይጀርያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ደብዳቤ ደርሶታል፤ ‘ሱፐር ኤግልስ’ በቀጣይ ሳምንት ለሚያካሂዷቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች አዲሱ የፋሲል ከነማ ፈራሚ ኦማስ ኦባሶጊን በስብስባቸው ማካተታቸው ተከትሎ ተጫዋቹ ሰኞ ነሐሴ ሀያ ሰባት ብሄራዊ ቡድኑ እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል።
በቅርቡ ፋሲል ከነማን የተቀላቀለው እና በቤንደል ኢንሹራንስ የመጨረሻ ዓመት ቆይታው የናይጀርያ ሊግ የወርቅ ጓንት አሸናፊ የሆነው ኦማስ ኦባሶጊን በውድድር ዓመቱ በአስራ ስምንት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር በመውጣት በናይጀርያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በአንድ የውድድር ዘመን በበርካታ ጨዋታዎች ግቡን ባለማስደፈር ክብረወሰን መጨበጡ ይታወቃል። አሁን ደግሞ ሀገሩ ናይጄሪያ ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከቤኒን እና ሩዋንዳ ለምታካሂዳቸው ጨዋታዎች መመረጡን ተከትሎ ከቀናት በኋላ ወደ ሀገሩ ያቀናል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ባሳየው አቋም በናይጄሪያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ካሉ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች ተርታ የተመደበው ይህ ተጫዋች ለቋሚ ተሰላፊነት ከስታንሊ ንዋባሊ እና ማዱካ ኦኮዬ ጋር የሚፎካከርም ይሆናል።