ከፍተኛ ሊግ | ሸገር ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሚሳተፈው ሸገር ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ወደ ቡድኑ አምጥቷል።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ሦስት ቡድኖችን በአንድ በማቀፍ ሸገር ከተማ በሚል በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ስር በመደልደል የመጀመሪያ ተሳትፎውን በሀገሪቱ ሁለተኛ ሊግ ዕርከን ያደረገው ክለቡ ዓመቱን በ33 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ያጠናቀቀ ሲሆን ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ይረዳው ዘንድ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል።

የክለቡ አዲስ አሰልጣኝ በመሆን የተሾመው በሽር አብደላ ነው ፤ በእግርኳስ ተጫዋችነቱ በነገሌ አርሲ ፣ ወልቂጤ ከተማ ፣ ሚዛን ቴፒ ፣ መቂ ከተማ እና ደደቢት በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን የአሁኑ አሰልጣኝ በጉዳት ከእግር ኳስ ከተገለለ በኋላ ለአምስት ዓመታት በነገሌ አርሲ የረዳት አሰልጣኝነት እንዲሁም ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ጥሩ ጊዜን አሳልፎ ቀጣዩ መዳረሻው ሸገር ከተማ ሆኗል።