18ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቀን ተቆርጦለታል

ለ18ኛ ጊዜ የሚደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በስድስት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል ከፊታችን ማክሰኞ አንስቶ ይደረጋል።

በየዓመቱ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዘንድሮም በስድስት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል እንደሚደረግ ሲታወቅ ፤ በዛሬው ዕለትም በራስ አምባ ሆቴል የዕጣ ማውጣት ስነስርዓቱ ተከናውኗል።

በዕጣ ማውጣት ስነስርዓት ላይ እንደተገለፀው ውድድሩ በአምስት የመዲናዋ ክለቦች እና በአንድ ተጋባዥ ቡድኖች መካከል ከፊታችን ማክሰኞ ነሃሴ 28 አንስቶ እስከ ጳጉሜ 5 ድረስ ለተከታታይ ስምንት ቀናት እየተደረገ እንደሚቆይ የከተማው ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

ውድድሩ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ የሚደረግ ሲሆን በምድብ አንድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ተጋባዡ ፋሲል ከነማ ሲደለደሉ በምድብ ሁለት ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ መቻል እና ኢትዮጵያ ቡና መደልደላቸው ሲገለፅ ውድድሩም በአበበ ቢቂላ እና በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚከናወንም ጭምር ተገልጿል።