ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ወደ ታዛኒያ ክለብ አምርተዋል

ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ወደ ታንዛኒያው ክለብ ማቅናታቸው ታውቋል።

በቅርብ ዓመታት በሴቶች እግርኳስ ከታዮ ጥሩ ተጫዋቾች መካከል እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በታንዛኒያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፈውን ያንግ አፍሪካንስ ለመቀላቀል መስማማታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ቡድኑን የተቀላቀለችው የመጀመሪያ ተጫዋች አርያት ኦዶንግ ናት። የእግርኳስ ሕይወቷን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የጀመረችው አጥቂዋ በተለያዩ የዕድሜ ዕርከኖች እና ዋናውን የሴቶች ብሔራዊ ቡድኑን ጨምሮ ለአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተጫወተች በኋላ ማረፊያዋ የታንዛኒያው ክለብ ሆኗል።

ሌላኛዋ ተጫዋች ንቦኝ የን ናት። ከጥሩነሽ ስፖርት አካዳሚ የተገኘችው አማካይ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተጫወተች በኋላ ዳግም ወደ ንግድ ባንክ ተመልሳ ስትጫወት እንደ አርያት ሁሉ በተለያዩ የዕድሜ ዕርከኖች እና በዋናው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጫውታ አሳልፋለች።