18ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ይካሄድ ይሆን?

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በስድስት ክለቦች መካከል ዛሬ ማክሰኞ ይጀምራል ቢባልም ከወዲሁ የተለያዩ ተግዳሮቶች በዝተውበታል።

ለአስራ ሰባተኛ ጊዜ በመካሄድ የረጅም ዓመት ታሪክ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ዘንድሮም ዘግይቶም ቢሆን በስድስት ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በማሳተፍ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር። ሆኖም ውድድሩ የመካሄዱ ነገር አጠራጣሪ የሚያደርጉ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከተለያዩ ምንጮቿ ያገኘቸው መረጃ ያመላክታል።

በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፍ ማረጋገጫ የሰጠው እና በምድብ ለ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከመቻል ጋር ተደልድሎ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና እንደማይሳተፍ ከደቂቃዎች በፊት ክለቡ ይፋ አድርጓል። ቡናማዎቹ በውድድሩ እንደማይሳተፉ ይግለፁ እንጂ በምን ምክንያት እንደሆነ ያልገለፁ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ለክለቡ ቅርበት ካላቸው አካላት እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ አብዛኛው የቡድኑ አባላት ወደ አሜሪካ እንደሚጓዙ ቢታወቅም በማይሄዱት አሰልጣኞች እና ቀሪ ተጫዋቾች የመዲናዋን ሲቲ ካፕ ለመሳተፍ ወስነው የነበረ ቢሆንም ትናንት ማታ በድንገት ውድድሩ ያለ ተመልካች በዝግ እንደሚካሄድ መወሰኑ እራሳቸውን ከውድድሩ ውጭ እንዲያደርጉ ከውሳኔ እንዳደረሳቸው ሰምተናል።

የውድድሩ ዓላማ ለክለቦችም ሆነ ለፌዴሬሽኑ ከተመልካች የሚገኝ ገቢ አንዱ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ትናንት ማምሻውን ድንገት ለውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ጨዋታዎቹ በዝግ እንዲያደርጉ ከበላይ አካል ትዕዛዝ መተላለፉ ሌላው ተግዳሮት ሆኖ ብቅ ብሏል።

አሁን ትኩረት የሚስበው ጨዋታዎቹ በዝግ መሆኑ እና ኢትዮጵያ ቡና ራሱን ከከተማው ዋንጫ ማግለሉን ተከትሎ ዛሬ እንደሚጀመር በሚጠበቀው ውድድር ቀሪ አምስት ቡድኖችን በመያዝ ይካሄዳል ወይ ወይስ አይካሄድም የሚለው ጉዳይ ነው።

ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካለቸው ምንጮቿ ባገኘችው መረጃ ከሆነ አዘጋጅ ኮሚቴው ኢትዮጵያ ቡና ከውድድሩ መውጣቱን እንደማያቁና ቀጣይ ጨዋታዎቹ የመካሄዳቸውን ነገር ውድድሩን በበላይነት ከሚመራው የከተማው ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ተነጋግረው ሊወስኑ እንደሚችሉ ሰምተናል።

ከኢትዮጵያ ቡና በተጨማሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርቡ ካለበት የአፍሪካ መድረክ ወሳኝ ጨዋታ አኳያ በተስፋ ቡድኑ ብቻ እንደሚጫወት መግለፁ እና ሌሎች ተግዳሮቶች ተጨምሮ የውድድሩን መካሄድ ነገር አጠራጣሪ አድርጎታል።

በዚህ ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎች ካሉ ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።