የቀድሞው የመድን ኮከብ በሁለት የስራ ዘርፍ ዋናውን ቡድን ተቀላቅሏል

የቀድሞው አጥቂ ከሀዲያ ሆሳዕና የቀናት ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ መድን ቡድን መሪ እና ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል።

ለ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን በአዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሲሠሩ ቆይተው ከወዳጅነት ጨዋታዎች መልስ በዛሬው ዕለት በትናንትናው ዕለት በአሰልጣኙ ለይኩን ታደሠ መሪነት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጅማሮ በፋሲል ከነማ 2ለ1 የተረቱት ኢትዮጵያ መድኖች የቀድሞ ስመ ጥር አጥቂያቸውን ወደ ዋናው ቡድን አካተውታል።

የኢትዮጵያ መድን ቡድን መሪ እና ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው መስፍን አህመድ (ጢቃሶ) ነው። ከ1990ዎቹ አጋማሽ አንስቶ በኢትዮጵያ መድን ፣ መቻል እና ንግድ ባንክ ረዘም ላሉ ዓመታት በአጥቂነት ያገለገለው የአሁኑ አሰልጣኝ በኢትዮጵያ መድን ከ17 ዓመት በታች ወጣት ቡድን ውስጥ ደግሞ ከ2003 እስከ 2016 አሰልጣኝ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን ከቀናቶች በፊትም በአሰልጣኝ ግርማ ታደሠ በሚመራው ሀዲያ ሆሳዕና ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሞ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ መድን ያደረገለትን ጥሪ ተከትሎ ሀዲያን በመተው ወደ ቀድሞ ክለቡ ቤት ተመልሷል።