የነብር እና የዋልያው ፍልሚያ በነብሮቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

በተውሶ በታንዛኒያው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም በአፍሪካ ዋንጫ የ2025 የማጣሪያ ጨዋታን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል።ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር ያለ ጎል ከተለያየችበት የባለፈው ጨዋታ ቢኒያም በላይ እና ወገኔ ገዛኸኝ ወጥተው በሱሌይማን ሀሚድ እና ሱራፌል ዳኛቸው ለውጥ ሲደረግባቸው ጊኒን 1ለ0 በረቱት ዲ አር ኮንጎዎች በኩልም በተደረገ ተመሳሳይ ቅያሪ ማሱዋኩ ካዌላ እና ኢዶ ካይንቤ አርፈው ቻድራክ አኮሎ እና ካኩታ ማምቤንጋ በምትካቸው ወደ ሜዳ ገብተዋል።


አልጄሪያዊው የመሐል ዳኛ ላህሉ ቤንብራሀም በመሩት የምሽቱ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ውስጥ  ተመሳሳይ የአጨዋወት ቅርፅን በሁለቱም በኩል ያስተዋልን ቢሆንም ማጥቃታቸው ግን በስልነት የታጀበ አልነበረም። እንደተለመደው በቅብብል ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ለማምራት መቆራረጦች ጎልቶ  የሚታይባቸው ዋልያዎቹ 4ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ሱራፌል አሻምቶ ፍሬዘር በግንባር ገጭቶ ኳሷ በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማዋን ሳትጠብቅ ከወጣችበት አጋጣሚ መልስ ዲ አር ኮንጎ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል።

በፈጣን ሽግግር ከመስመር መነሳትን የመረጠው ቡድኑ ከሳጥን ጠርዝ ሳሙኤል ኤሴንዴ በቀጥታ አክርሮ የመታትን ኳስ ሰይድ ሀብታሙ በግሩም ቅልጥፍና ከመረቡ ጋር እንዳትገናኝ አግዷታል። ከነዓን ማርክነህን ከተፈጥሯዊ ቦታው ፊት ላይ ማጫወትን የመረጡት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ቡድናቸው ከሚያደርገው አንድ ሁለት ንክኪ በኋላ አጥቂን ያማከሉ ኳሶች ላይ ሲገኙ ከነዓን በጥልቀት ወደ አማካይ ክፍል ሲሳብ መስተዋሉ ቦታው ላይ በይበልጥ ክፍተቶችን እንዲስተዋሉ ሆኗል። ኳስን ሲያገኙ በቁጥር በዛ በማለት በእንቅስቃሴ የዋልያዎቹ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ይደርሱ የነበሩት ነብሮቹ በቀላሉ የተከላካይ መስመርን በማለፍ ከሰይድ ጋር መገናኘት ከብዷቸው ተስተውሏል።

22ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የአንድ ሁለት እግር ሥራ ጋቶች ወደ ግራ የጣለውን ኳስ ነፃ ሆኖ ያገኘው ያሬድ ካሳዬ ወደ ውስጥ አሻምቶ ከነዓን ያመለጠችውን ኳስ በረከት ሲመታት ካሜምቤ ተደርቦ ኳሷን አውጥቷል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሄንዴክ አኖንጋ የተሳሳተውን ኳስ ብርሃኑ ከሱራፌል ጋር ተቀባብሎ በመጨረሻም ክፍት ቦታን ያገኘው ብርሃኑ በሚያስቆጭ ቸልተኛ ምት ኳሷን ቢመታም ዒላማ አልባ ሆናበታለች። ጨዋታው 41ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከርቀት ዲ ኤር ኮንጎዎች በቻርለስ ፒክል አማካኝነት ካደረጓት ሙከራ በኋላ 0ለ0 ተጋምሷል።

 

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ዲ.አር. ኮንጎዎች እንቅስቃሴዎቻቸውን በኮሪደሮች በኩል በሰላ አጨዋወት መንቀሳቀሳቸውን ከጀመሩ በኋላ በተወሰነ መልኩ ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአንፃሩ እንደተለመደው ቅብብል ላይ ለማተኮር ያደረጉት ጥረት በዚህኛው አጋማሽ ለስህተት ተጋላጭ እንዲሆኑ ዳርጓቸዋል። 56ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ የተሳሳተውን ኳስ ጃሪስ ካዬምቤ ነጥቆ የሞከረውን ሰይድ የተቆጣጠራት ሲሆን በተመሳሳይም ከአንድ ደቂቃ በኋላ ጋቶች የፈጠረውን የማቀበል ስህተት ዊሳ አግኝቶ ወደ ግብ ቢሞክርም ሰይድ ዳግም ኳሷን በእቅፉ ከቷታል።

ከመስመር ሲነሱ አስፈሪነታቸው እየጨመረ የመጣው ዲ አር ኮንጎዎች በ62ኛው ደቂቃ የመሪነት ግባቸውን አግኝተዋል። ከግራ ከዊሳ ጋር ተቀባብሎ ጄሪስ ካዬምቤ ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው የስፓርታ ሞስኮው አጥቂ ቲዮ ሞንጎንዳ መረብ ላይ አሳርፏታል። ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ቸርነት እና በረከትን በቢኒያም በላይ እና አብነት ደምሴ ቅያሪ ያደረጉት ዋልያዎቹ እንደ ቅያሪያቸው ሜዳ ላይ የፈጠሩት አንዳች ነገር ግን አልነበረም ይልቁንም 76ኛው ደቂቃ ላይ ሜሻክ ኤልያ ከማዕዘን ያሻማለትን ኳስ ፊስተን ማዬሌ በግንባር ገጭቶ ነብሩን 2ለ0 አድርጓል። በጭማሪ ደቂቃ ኢትዮጵያ ምንይሉ ወንድሙ ካደረጋት ሙከራ በኋላ ጨዋታው ተጨማሪ ነገሮችን ሳያስመለክተን በዲ. አር. ኮንጎ አሸናፊነት ድምዳሜን አግኝቷል።