“በጨዋታው መፍትሄ ለማግኘት ትንሽ ሰዓት ወስዶብን ነበር። ግን መፍትሔ በመስጠት ጨዋታውን አሸንፈናል”

ትናንት ምሽት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ያሸነፉት የኮንጎ ዲ.አር አሠልጣኝ ሴባስቲን ዲሴበር ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው...

ከጨዋታው በፊት እንዳልኩት ፈታኝ ጨዋታ ነበር። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ጊዜ ነበረን። በመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ታክቲካዊ ችግሮች ነበሩብን። በጨዋታውም ይሄንን ለማስተካከል ሞክረናል። በአጠቃላይ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፋችን በጣም ደስተኛ ነን። በሁለቱም ጨዋታም ግብ አላስተናገድንም። በዚህም ደስተኛ ነን።

ከተጠባባቂ ወንበር በተነሱ ተጫዋቾች ጨዋታውን ስለማሸነፋቸው…

ሁላችንም የአንድ ቡድን አባላት ነን። 11 ተጫዋቾች ጨዋታ ቢጀምሩም ጨዋታው ላይ የሚፈጠሩትን ነገሮች በመንተራስ ለውጦች ይፈጠራሉ። ልክ ነው ቲዮ ቦንጎንዳ አስቆጥሯል ግን እሱም የቡድኑ አባል ነው። ቡድኑ ነው ያሸነፈው። የቡድናችን ስሜት በጣም ከፍተኛ ነው። ሁሉም የቡድኑ አባላት ፕሮፌሽናል ናቸው። በጨዋታው መፍትሄ ለማግኘት ትንሽ ሰዓት ወስዶብን ነበር። ግን መፍትሔ በመስጠት ጨዋታውን አሸንፈናል።

ስለቡድናቸው እንቅስቃሴ…

ትልቁ አስፈላጊ ነገር ውጤቱ ነው። ሁሉም አሠልጣኞች ጨዋታዎችን በጥሩ እንቅስቃሴ ከውነው አሸንፈው መውጣት ይፈልጋሉ። ግን ይሄ አንዳንዴ አስቸጋሪ ነው። በሁለቱን ጨዋታዎች ጠንካራ ፈተና ሜዳ ላይ ገጥሞናል። ግን ሁለቱንም አሸንፈናል። በዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ ሁለት ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በኢትዮጵያ በኩል አስተናግደን ነበር። ምናልባት ሊገባብን ይችል ነበር። ግን ጠንካራ የተከላካይ መስመር ነው ያለን። ጥሩ እግርኳስም ከአየር ንብረቱ ጋር እየታገልን ለመጫወት ሞክረናል። በዛሬው ጨዋታ የተወሰነ ለውጦችን አድርገን እድገቶች አሳይተናል። በቀጣይ በጥቅምት ወር ከታንዛኒያ ጋር ላለብን ጨዋታ ዝግጅታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።