ወሳኙን የባንክ እና ያንግ አፍሪካስ ጨዋታ የሚመሩ አልቢትሮች ታውቀዋል

ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ እና ታንዛኒያን ጨዋታ የመሩት ሦስት ዳኞች የፊታችን ቅዳሜ የሚደረገውን የባንክ እና ያንግ አፍሪካንስ ጨዋታ እንዲመሩ ተመድበዋል።

የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ በተለያዩ የአህጉራችን ክፍሎች የሚደረጉ ሲሆን የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነውና በአህጉራዊ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር የዩጋንዳውን ቪላ ክለብ በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፊታችን ቅዳሜ የዙሩን የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳው ያከናውናል። ባንክ ከታንዛኒያው ኃያል ክለብ ያንግ አፍሪካስ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ደግሞ ሴኔጋላዊ አልቢትሮች እንዲመሩ ምደባ መደረጉ ታውቋል።

የዛሬ ሳምንት ረቡዕ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም በኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የተደረገውን ጨዋታ የመሩት ዋና እና ረዳት ዳኞችም ይህንን የባንክ እና ያንጋ ጨዋታ እንዲመሩ መመደቡ ተመላክቷል።

በዚህም ጨዋታውን በመሐል አልቢትርነት ኢሳ ሲ ከረዳቶቻቸው ጂብሪል ካማራ እና ኖሀ ባንጉራ እንዲሁም አራተኛ ዳኛው ዳውዳ ጉዬ ጋር በመሆን ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ያንግ አፍሪካስ ጨዋታ ቅዳሜ መስከረም 4 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል።