የ2016 የዓመቱ ኮከቦች ሽልማት የሚካሄድበት ቀን ታውቋል

ከወትሮ መዘግየት ያሳየው የ2016 የዓመቱ የኮከቦች ሽልማት መርሐግብር የሚካሄድበትን ቀን እና ቦታ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

በሊጉ አክሲዮን የበላይነት ከውድድር ዓመቱ መጠናቀቅ በኋላ በተለያዩ ዘርፎች የሚካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ኮከብ ሽልማት መርሐግብር የዘንድሮው መዘግየት ማሳየቱን እና የሽልማቱንም ድባብ እንዳደበዘዘው የሊግ አክሲዮን ማኅበሩ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ አናግረን መቼ ሊካሄድ እንደታሰበ ከዚህ ቀደም አንድ መረጃ አጋርተናችሁ ነበር።

ሶከር ኢትዮጵያ ከውስጥ ምንጮቿ ባደረገችው ማጣራት መርሐግብሩን ሁሉን ተሳታፊ ክለቦች በሚገኙበት ድሬደዋ ከተማ ላይ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ዘግባም ነበር። አሁን ባገኘነው መረጃ ጥረቱ ተሳክቶ የሽልማት ፕሮግራሙ መስከረም ዘጠኝ ቀን በድሬደዋ ከተማ ካፒታል ቢ ሆቴል ምሽት አስራ ሁለት ሰዓት ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙን አረጋግጠናል።

ይህ ዝግጅት በድሬዳዋ ከተማ በደማቅ ሁኔታ እንዲካሄድ የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስፈላጊውን ነገር ሁሉ በማሟላት ሙሉ ድጋፍ ያደረገ መሆኑን የሰማን ሲሆን የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ አባላት የከተማው አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ከዚህ ቀደም ድሬዳዋ ከተማ ውድድሮችን በብቃት ማዘጋጀታቸው እና አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ የሚታወቁ በመሆናቸው አውስተው የሽልማት ፕሮግራሞችን ከአዲስ አበባ በማውጣት ወደ ክልል እንዲደረግ በማሰብ ድሬዳዋን መመረጣቸውን  አውቀናል።