ነብሮቹ የወሳኝ አጥቂያቸውን ውል አራዝመዋል

የሀዲያ ሆሳዕና የመስመር አጥቂ ለተጨማሪ ዓመት በቡድኑ የሚያቆየውን ውል አራዝሟል።

የውል ዘመኑ መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ግብፁ ክለብ አል – መስሪ እንደሚጓዝ ተነግሮለት የነበረው የመስመር አጥቂው ተመስገን ብርሃኑ የዝውውሩ ሂደት በአንዳንድ ነገሮች ከስምምነት አለመድረሱን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት መመለሱ ይታወቃል።

ወደ ሀገር ቤት መመለሱ ዜና ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ክለቦች ሲፈለግ የቆየው የመስመር አጥቂው በመጨረሻም በአሳዳጊ ክለቡ ለተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት መስማማቱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ለነብሮቹ ላለፉት አራት ዓመታት ከ20 ዓመት በታች ቡድን ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ግልጋሎት የሰጠው ተመስገን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሰባት ጎሎች በማስቆጠር ጥሩ ጊዜ ከማሳለፉ ባሻገር የዓመቱ ወጣት ተስፈኛ ተጫዋች ዕጩ ውስጥ መካተቱ ይታወቃል።

ለሀዲያ ለሁለት ዓመት ለመጫወት የተስማማው ተጫዋቹ የሕክምና ምርመራውን በማጠናቀቅ በቅርቡ ፊርማውን በይፋ እንደሚያኖር ይጠበቃል።