ፈረሰኞቹ ዩጋንዳዊውን በውሰት ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል

ዩጋንዳዊው የመሀል ተከላካይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማቅናት ከጫፍ ደርሷል።

በክረምቱ በርከት ያሉ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ማጣታችውን ተከትሎ ቡድናቸውን ለማጠናከር በዝውውር መስኮቱ በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾች ያስፈረሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በትናንትናው ዕለት ወጣቱን አጥቂ ፉዓድ አብደላን ማስፈረማቸው የሚታወስ ሲሆን ፤ አሁን ደግሞ ዩጋንዳዊው የመሀል ተከላካይ ጊፍት ፍሬድን በውሰት ለማስፈረም ከስምምነት እንደደረሱ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ቦማ በተባለ ክለብ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው እና በዩጋንዳው ቪላ የሦስት የውድድር ዘመናት ቆይታ የነበረው ይህ የሀያ ስድስት ዓመት ተከላካይ ባለፈው የውድድር ዓመት በሦስት ዓመት ኮንትራት ወደ ታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ቢያቀናም በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቂ የመሰለፍ ዕድል ባለማግኘቱ ቀሪ የሁለት ዓመታት ውል እያለው ክለቡን ለቆ በውሰት ፈረሰኞቹን ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል።


በቪላ ቆይታው ቡድኑን በአምበልነት መምራት የቻለው ፍሬድ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ለሀገሩ ዩጋንዳ አምስት ጨዋታዎች ማድረግ የቻለ ሲሆን በ2022 ቻን አፍሪካ ዋንጫም ተሳታፊ ነበር።