ግርማ በቀለ ወደ ልጅነት ክለቡ ተመልሷል

ሀዋሳ ከተማ ሁለገቡን ተጫዋች የግሉ ሲያደርግ የአጥቂውን ውልም አራዝሟል።

በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመሩ በመቀመጫ ከተማቸው የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሲሠሩ የከረሙት ሀዋሳ ከተማዎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት እስከ አሁን አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረሙ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ግርማ በቀለን የስብስባቸው አካል አድርገዋል።

እግር ኳስን ከሀዋሳ ከተማ ከጀመረ በኋላ በሁለት አጋጣሚዎች ዋናውን ቡድን ጭምር ያገለገለው የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና የተከላካይ እንዲሁም የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች ወደ ሀድያ ሆሳዕና አምርቶ ሦስት የውድድር ዘመናትን ካሳለፈ በኋላ ዳግም ወደ ልጅነት ክለቡ ሀዋሳ ለሦስተኛ ጊዜ የሚመልሰውን ዝውውር አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታን በደርቢ መርሐግብር ከሲዳማ ቡና ጋር የሚጫወቱት ኃይቆቹ የአጥቂው ቸርነት አውሽን ኮንትራት ለተጨማሪ ዓመት አራዝመዋል።