በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመልስ ጨዋታቸውን ለማድረግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቡድን አባላት ነገ ወደ ዛንዚባር ይጓዛሉ።
በመጀመርያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸው የዩጋንዳውን ቪላን በመርታት ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር በመደልደል ባሳለፍነው ቅዳሜ የመጀመርያ ጨዋታቸውን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በያንጋ 1ለ0 የተረቱት ንግድ ባንኮች በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን የመቀልበስ ከባድ የቤት ሥራቸውን ለመወጣት ነገ ወደ ዛንዚባር እንደሚያቀኑ ታውቋል።
ከመጀመርያው ጨዋታ ማግስት ጀምሮ ልምምዱን በቢሾፍቱ የሠራው ቡድኑ ዛሬ የሀገር ቤት የመጨረሻ ልምምዱን ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አከናውኗል። አንድ ሰዓት ተኩል በቆየው የዛሬው ልምምድ በዋናነት ከኳስ ጋር ያተኮረ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሲከውኑ ነበር። ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት እንደሚገኙ ሲነገር ቡድኑ ዛንዚባር ከደረሰ በኋላ ባሉት ሦስት ቀናት ልምምዱን በዛው እንደሚሠራ ሰምተናል።
አስራ ሰባት ተጫዋቾችን ጨምሮ ከ22 የማይበልጡ አባላትን በመያዝ ነገ ረፋድ ላይ ወደ ዛንዚባር የሚጓዙ ሲሆን ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ያለፉትን የዝግጅት አንድ ወራትን በውስጥ ስምምነት ፈፅመው አብረው ሲሰሩ የቆዩት ተከላካዩ ፍቃዱ ደነቀው፣ የመስመር አጥቂው አብዱልለጢፍ ሙራድ እና አማካዩ ብሩክ ብፁአምላክ ከቡድኑ ጋር እንደተለያዩ ሰምተናል።
የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ በቀጣዩ ቅዳሜ በዛንዚባር አማኒ ኮምፕሌክስ ስታዲየም ምሽት ላይ የሚደረግ ይሆናል።