ምዓም አናብስት ቡድናቸውን ማጠናከር ቀጥለውበታል

መቐለ 70 እንደርታ አማካዩን ለማስፈረም ተስማምቷል።

ቀደም ብለው ጋናውያኖቹን ኮዲ ኮርድዚ እና ቤንጃሚን አፉቲ ያስፈረሙት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ ተጨማሪ አማካይ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል። ቡድኑን ለመቀላቀል ከስምምነት የደረሰው ተጫዋች ደግሞ ላለፉት ሳምንታት ከክለቡ ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅት በማድረግ ላይ የቆየው ኪሩቤል ኃይሉ ነው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ካፈራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው እና እግር ኳስን በሚማርበት ትምህርት ቤት በደብረ ሠላም ካቶሊክ ትምህርት ቤት ፕሮጀክት የጀመረው ይህ አማካይ የአራት ዓመታት የአካዳሚ ቆይታውን ካጠናቀቀ በኋላ ለኢኮስኮ፣ ደሴ ከተማ እና ፋሲል ከነማ መጫወት የቻለ ሲሆን ባለፉት ዓመታትም ከሀገር ውጭ በአሜሪካን ሀገር ቆይታ ካደረገ በኋላ በድጋሚ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ለመቐለ 70 እንደርታ ለመጫወት ከስምምነት ደርሷል።