የዋልያዎቹ አለቃ የብሔራዊ ቡድን ቆይታ ?

የውል ዘመናቸው ሊጠናቀቅ የተቃረበው አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ በቆይታቸው ዙርያ ምን አዲስ ነገር ተሰምቶ ይሆን ?

በ2016 መጀመርያ ላይ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እንዲሆኑ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ መሾማቸው ይታወሳል። በቅርቡ የውል ዘመናቸው የሚገባደድ መሆኑን ተከትሎ በቀጣይ በኃለፊነት ይቀጥላሉ ወይስ ዋልያዎቹ ሌላ አዲስ አሰልጣኝ ያገኛል የሚለው ትኩረት የሚስብ ዜና ሆኗል።

በትናንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከሚዲያ አካል
ስለ ወደ ፊት ቆይታቸው ዙርያ ጥያቄ የተነስቶላቸው ምላሽ የሰጡት አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ “ በቅርቡ ኮንትራቴ ይጠናቀቃል ጊዜው ሲደርስ ይፋ የሚሆን ይሆናል።” በማለት ምላሽ እንደሰጡ እና “ለብሔራዊ ቡድንም ሆነ ለክለብ መስራት ሰልችቶኛል በሁለት ኃላፊነት መቆየት ከድካም ውጪ ምንም ያገኘሁበት ነገር የለም”ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

በሌላ በኩል ሶከር ኢትዮጵያ የእግርኳሱ የበላይ አካል ወደ ሆነው ፌዴሬሽን በአሰልጣኙ ቆይታ ዙርያ ምን እየታሰበ እንደሆነ ለማጣራት ያደረገችው ጥረት ለጊዜው ባይሳካም ከውስጥ ምንጮቿ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ በትናትናው ዕለት በብሔራዊ ቡድኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ዙርያ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ሰፊ ግምገማ ማድረጋቸውን የሰማን ሲሆን በተጨማሪም አሰልጣኙ ትናንት ረፋድ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በተናገሩት ንግግሮች ደስተኞች እንዳልሆኑ ሰምተናል።

አሁን የሚጠበቀው በትናትናው ግምገማ መነሻነት አሰልጣኙ ውላቸውን አራዝመው ይቀጥላሉ ወይስ ይሰናበታሉ የሚለው ጉዳይ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ከታማኝ ምንጮቿ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የአሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ እና የዋልያዎቹ እህል ውሃ ያበቃለት ይመስላል። ፌዴሬሽኑ በቀጣይ በሚሾሙት አሰልጣኝ ዙርያ እያሰበ ሲሆን ምን አልባት ፊቱን ወደ ውጭ ሀገር አሰልጣኝ ሊያዞር እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አሰልጣኙ በብሔራዊ ቡድን በቆዩበት አንድ ዓመት ውስጥ ካደረጓቸው ስድስት የነጥብ ጨዋታዎች አንድም ጨዋታ ያላሸነፉ ሲሆን በአራት አቻ፣ በሁለት ሽንፈት፣ አንድ ጎል አስቆጥረው፣ ስድስት ጎል አስተናግደዋል።