የቅጣት ምት መቺው ግብ ጠባቂ ጎል አስቆጥሯል

እየተደረገ በሚገኘው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና ክልሎች ሻምፒዮና ላይ እያስገረመ የሚገኘው ግብ ጠባቂ…!

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚደረገው የ2016 የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና ክልሎች ሻምፒዮና በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ የምድብ ጨዋታዎች እየተገባደዱ ይገኛሉ። በምድብ “ሀ” የተደለደለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ትላንት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን 5ለ0 በሆነ ውጤት ሲረታ በጨዋታው ላይ አንድ ክስተት መመልከት ችለናል።

በዓለማችን እግር ኳስ ላይ የቆሙ ኳሶችን በተለይ ጎል አካባቢ የተገኙ የቅጣት እና የማዕዘን ምቶችን የሚመቱት ሜዳ ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ቢሆኑም በዚህ ውድድር ላይ ባልተለመደ መልኩ በምድቡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሁሉ ጎል አካባቢ የተገኙ እንዳሁም ቡድኑ የሚያገኛቸውን የማዕዘን ምቶች የሚመታው የቡድኑ ግብ ጠባቂ ብሩክ ዘላለም መሆኑ በእግር ኳሱ ያልተለመደ ተግባር መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ መታዘብ ችላለች።

በተደጋጋሚ በቡድኑ አሰልጣኝ የቆሙ ኳሶችን እንዲመታ ሲደረግ የነበረው ይህ ግብ ጠባቂ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በትላንትናው ዕለት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ላይ ካስቆጠሯቸው አምስት ግቦች መካከል የመጀመሪያዋን ግብ ከሳጥን ጠርዝ ከተገኘ የቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ ከመረብ ማሳረፉ በበርካቶች ዘንድ ያልተለመደ መሆኑን ተከትሎ እያስረገመ የሚገኝ ተግባር ሆኗል።