ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ይቀጥላል ?

ከሰዓታት በፊት በመክፈቻ የሊግ ጨዋታቸው ለመቻል ፎርፌ ለመስጠት የተገደዱት ወልቂጤ ከተማዎች አሁናዊ ሁኔታ…..

ባለፈው የውድድር ዓመት በተለያዩ ችግሮች ተፈትነው በሊጉ ላይ የቆዩት ወልቂጤ ከተማዎች በአዲሱ የውድድር ዓመት አስፈላጊውን የክለብ ላይሰንሲንግ መመዘኛዎች ባለማሟላታቸው የሊጉን የመጀመርያ ጨዋታ በፎርፌ መሸነፋቸው መግለፃችን ይታወሳል ፤ በዚህ መነሻነት ሶከር ኢትዮጵያ በክለቡ አሁናዊ ሁኔታ እና ቀጣይ ዕጣ ፋንታ በተመለከተ ከክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ሞሳ አብራር ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ክለቡ በሊጉ ላይ የመቀጠሉ ጉዳይ አስመልክተን ላነሳንላቸው ጥያቄ ቡድኑ በሊጉ ላይ እንደሚቀጥል እና ችግሩን ለመፍታት ቀደም ብለው ስራዎች እንደጀመሩም ገልፀዋል ፤

” ከሁለት የውጭ ተጫዋቾች ደሞዝ ጋር በተያያዘ ፊፋ ያቀረበብንን ክስ ለመፍታት የአንዱን ተጫዋች ውዝፍ ዕዳ ከፍለናል ፤ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች የአራት ወር ደሞዝም በአንድ ወር ወስጥ እንከፍላለን ለዚህም ደብዳቤ ፅፈናል ሌሎች ከኢንሹራንስ እና ህክምና ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እንዳንፈታም በእግዱ ምክንያት ምንም አይነት ግልጋሎት እያገኘን አይደለም። ህጉ ትክክል ሊሆን ይችላል ግን ዕዳው በአንድ ጊዜ መክፈል ከባድ ነው ፤ አሁን ባለው የሀገራችን እግር ኳስ ሁኔታ ይህንን ማድረግ ከባድ ነው” ካሉ በኋላ ፌደሬሽኑ ይህንን ተገንዝቦ ችግሩን ለመፍታት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጥያቄ በማቅረብ ከዚህ ቀደምም በተለያዩ መንገዶች ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይም ክለቡ በመጪው ረቡዕ መስከረም 15 ምሸት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከመግጠሙ አስቀድሞ በሚኖሩት ጥቂት ቀናት የሚጠበቅበትን አሟልቶ ይመዘገባል ወይ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።