ሪፖርት | ዐፄዎቹ በመጨረሻ ደቂቃ በተገኘች ግብ ፈረሰኞቹን ረተዋል

በምሽቱ ጨዋታ ፋሲል ከነማ በሁለቱ አጋማሾች ባስቆጠሯቸው ጎሎች ቅዱስ ጊዮርጊስን 2ለ1 ረተዋል።


ሁለቱም ቡድኖች በክረምቱ ካደረጓቸው ዝውውሮች ውስጥ በተመሳሳይ ሦስት ተጫዋቾችን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተጠቅመው በጀመሩት ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን ሀያ አምስት ደቂቃዎች ፋሲል ከነማዎች አንፃራዊ ብልጫን ወስደው መንቀሳቀስ ችለዋል።

ወደ ጨዋታ ለመግባት እጅጉን ተቸግረው የነበሩት ፈረሰኞቹ 20ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል ፤ አማኑኤል ተርፉ በግራ የሜዳው ክፍል ማርቲን ኪዛ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ቢኒያም ላንቃሞ ግሩም አድርጎ ባህሩ መረብ ላይ አሳርፏታል።

31ኛው ደቂቃ ላይ ማርቲን ኪዛ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ በግራ እግሩ መቶ ባህሩ ካዳነበት በኋላ የቀሩትን ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጫና የፈጠሩበት ሆኗል።

በሁለት ንክኪ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል በድግግሞሽ የደረሰው ቡድኑ በመስመር አልያም ከቆሙ ኳሶች መነሻ የማጥቂያ መንገዳቸው ሆኖ መመልከት ብንችልም በተጫዋቾች ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ አጋጣሚዎችን በቀላሉ ሲያመክኑ ተስተውሏል።

ከዕረፍት መልስ በይበልጥ ተመጣጣኝ መልክ በነበረው ጨዋታ ሜዳ ላይ የሚደረጉ ቅብብሎች ተባረክተው የታዩበት ከመሆን በዘለለ በሙከራዎች እምብዛም መታጀብ አልቻለም። ፈረሰኞቹ አጫጭር ቅብብልን መርጠው በሚጫወቱበት ወቅት በተሻለ በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫን መውሰድ ሲችሉ በአንፃሩ ወጥነት አይኑረው እንጂ ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን መርጠው የሚንቀሳቀሱት አፄዎቹ በበኩላቸው ማርቲን ኪዛን ላይ ያተኮሩ ጥቃቶችን ምርጫቸው አድርገው ተመልክተናል። በአጋማሹም የጠራ አጋጣሚን ለመመልከት የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ለመጠበቅ የተገደድን ሲሆን በዚህም 84ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ ወደ አቻነት መጥተዋል።

ተቀይሮ የገባው እዮብ ማቲያስ ሳጥን ውስጥ በረከት ወልዴ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሁለት ጊዜ ለመምታት የተገደደው ፍፁም ጥላሁን ከመረቡ በማዋሀድ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል።

ጨዋታው ቀጥሎ 87ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ፋሲሎች ዳግም መሪ ሆነዋል። ከማዕዘን ቃልኪዳን ዘላለም ያሻማውን ኳስ ምኞት ደበበ በግንባር ገጭቶ የቀድሞው ክለቡ ላይ በማስቆጠር በመጨረሻም ጨዋታው በአፄዎቹ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ድክመት እንደነበረባቸው ጠቅሰው የተጫዋቾቹ ልምድ ማጣት በውድድር ዓመቱ ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችል በመጠቆም በዳኝነቱ ላይ አስተያየት ከመስጠት ሲቆጠቡ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው በብዙ ምክንያቶች ዛሬ ያስቆጠሯቸው ጎሎች የተለየ ደስታ እንደፈጠሩላቸው እና ጨዋታውን ከመቆጣጠር አንጻር የተጫዋቾቻው እንቅስቃሴ ጥሩ እንደነበር በመናገር ከቆሙ ኳሶች አጠቃቀም አኳያ የመረጧቸው ተጫዋቾች አፈጻጸም የተሳካ እንደነበር ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።