አዳማ ከተማ ሦስቱን አምበሎች አሳውቋል

የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊው አዳማ ከተማ የአምበሎቹን ዝርዝር ለሶከር ኢትዮጵያ ይፋ አድርጓል።

በባቱ ከተማ አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን ይዘው የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሲሰሩ ቆይተው ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ የከተሙት በአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች በዛሬው ዕለት ከቀትር መልስ ስሑል ሽረን ከመግጠማቸው በፊት የቡድናቸውን ሦስት አምበሎች ዝርዝር ለሶከር ኢትዮጵያ በላኩት መረጃ ጠቁመዋል።

ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው የቀድሞው የባህር ዳር ከተማ ፣ ወልዲያ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ መቐለ ፣ ድሬዳዋ ፣ እና ወልቂጤ የተከላካይ አማካዩ ዳንኤል ደምሱ ቡድኑን በዋና አምበልነት እንዲመራ የተመረጠ ሲሆን ወጣቱ አጥቂ ቢኒያም ዐይተን እና ከመቻል ቡድኑን የተቀላቀለው ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ የቡድኑ ሁለተኛ እና ሦስተኛ አምበል ሆነው ተመርጠዋል።