ቀይ ቀበሮዎቹ በአውሮፓ የታዳጊ ቡድኖች የሚጫወቱ ወጣቶችን በስብስባቸው አካተቱ

በስፔን እና ኦስትሪያ ታዳጊ ቡድኖች የሚጫወቱ ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ይሳተፋሉ ።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ዞን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የሚያደርገውን ዝግጅት ከጀመረ ስድስት ቀናትን አስቆጥሯል። ቡድኑ የመጨረሻ ስብስቡን ይፋ ከማድረጉ በፊት ወደ ውድድር የሚያቀኑ ተጫዋቾች እየለየ ሲገኝ ሁለት ተጫዋቾችን ከአውሮፓ አካትቶ ወደ ስፍራው እንደሚያቀና ሶከር ኢትዮጵያ ሰምታለች።

ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ተጫዋቾችም ከስፔኑ ‘B One’ አካዳሚ ተመርጦ ከቀናት በፊት ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀለው ይበልጣል ኤልያስ እና በኦስትርያው ቪየና ሁለት የሚጫወተው አእላፍ አያሌው ናቸው። በሶዶ ከተማ ተወልዶ በትውልድ አካባቢው እግር ኳስ የጀመረው እና ከአንድ ዓመት በፊት በስፔኗ ካታላን ግዛት ወደ ሚገኘው ‘B one’ አካዳሚ ያቀናው ይበልጣል ኤልያው በአንድ ዓመት የስፔን ቆይታው በተለያዩ ውድድሮች መሳተፍ ከቻለ በኋላ ደግም ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ብሔራዊ ቡድኑን ያገለግላል።

ሁለተኛው ከኦስትርያው ቪየና ሁለት ብሔራዊ ቡድኑን የሚቀላቀለው በአማካይነት እና በአጥቂነት የሚጫወተው ላለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የታዳጊዎች ውድድር ድንቅ ብቃቱን በማሳየት የሚገኘው የአስራ ስምንት ዓመቱ አእላፍ እያሌው ነው። ከዚህ ቀደም በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ማሰልጠኛ ማዕከል፣ በሱሳ ቪየና፣ ቪየና የታዳጊዎች እና ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ቡድን ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቪየና ሁለት በመጫወት ላይ ያለው ተስፈኛው በኦስትርያ ቆይታው ባደረጋቸው 79 ጨዋታዎች 81 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል። ተጫዋቹ በነገው ዕለት ብሔራዊ ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎም ይጠበቃል።

በታንዛንያ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የሴካፋ ዞን ከሃያ ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በዝግጅት ላይ የሚገኘው በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ዕለት ስብስቡን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።