ሪፖርት|  ሮዱዋ ደርቢ በኃይቆቹ አሸናፊን ተገባደደ

ሀዋሳ ከተማዎች የውድድር ዓመቱን በድል ጀምረዋል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ትላልቅ ግዢዎችን   ባደረጉ ሁለት ክለቦች መካከል የተካሄደው የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሐግብር በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢያስመክትም በሂደት ሲዳማ ቡናዎች መጠነኛ ብልጫ ወስደዋል። በአጋማሹ በአመዛኙ ረዣዥም ኳሶች እንዲሁም በፈጣን ሽግግር የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሞከሩት ኃይቆቹ ዓሊ ሲሌይማን አክርሮ መቶት ወደ ውጭ ከወጣው ሙከራ በኋላ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ አላደረጉም። በአንፃሩ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ሲዳማዎች በመስፍን ታፈሰ ሦስት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ፈጣኑ አጥቂ ሬድዋን ናስር ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ሞክሮት ሰይድ የተቆጣጠረው ሙከራ እና ከሳጥን ውጭ የሞከራቸው ሙከራዎችም የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በ42ኛው ደቂቃ ግን በአጋማሹ ጠንካራ የሚባል የግብ ዕድል ያልፈጠሩት ሀዋሳ ከተማዎች በተባረክ ሄፋሞ አማካኝነት መሪ መሆን ችለዋል። በውድድር ዓመቱ የክለቡን የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረው አጥቂው፤ እስራኤል እሸቱ ከፈቃደሥላሴ የተቀበላትን ኳስ በፈጣን ሽግግር ወደ ሳጥን ካሻገራት በኋላ አግኝቶ ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው። የሲዳማ ቡና የኳስ ቁጥጥር እና የሙከራ ብልጫ የሀዋሳ ከተማ ጠንካራ መከላከል እና የተለመደው የፊት መስመር ውጤታማነት የታየበት አጋማሽም በኃይቆቹ መሪነት ተገባዷል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ መልክ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ በሲዳማ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢቀጥልም እንደወሰዱት ብልጫ የሀዋሳ ከተማን የመከላከል አደረጃጀት አልፈው በርከት ያሉ ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም። ሆኖም በ58ኛው ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሀብታሙ ታደሰ መስፍን ታፈሰ ከመስመር አሻግሮት ተከላካዮች የጨረፉትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በሰይድ ሀብታሙ ድንቅ ብቃት አግዳሚውን ለትማ የተመለሰች ኳስም ሲዳማን አቻ ለማድረግ የተቃረበች የግብ አጋጣሚ ነበረች። በሂደት በተጋጣሚ የግብ ክልል ላይ አደጋዎች መፍጠራቸውን የቀጠሉት ሲዳማዎች ከሙከራው በኋላም ሌላ የግብ ሙከራ አድርገዋል። በጨዋታው በግሉ በርከት ያሉ ሙከራዎችን ያደረገው መስፍን ታፈሰ ከማዕዘን ተሻግራ አበባየሁ ሀጂሶ ያመቻቻትን ኳስ መትቶ ሰይድ ሀብታሙ በሚያስደንቅ ብቃት አምክኗታል።

የሲዳማ ቡና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና የመስፍን በርካታ ሙከራዎች እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያስመለከተን ጨዋታም በኃይቆቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሀሳባቸውን የሰጡት የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ተጋጣሚያቸው ጥቅጥቅ ብሎ ለመከላከል እንደመረጠ ከገለፁ በኋላ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተሻሉ እንደነበር ጠቅሰው የመከላከል አደረጃጀቱን አልፎ ዕድሎች በመፍጠር እና ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ክፍተት እንደነበረባቸው አንስተዋል። የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው ውጤቱን አጥብቀው መፈለጋቸውን ከገለጹ በኃላ መከላከሉ ላይ ጥሩ እንደተንቀሳቀሱ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም የግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙን ብቃት አድንቀው አጠቃላይ ቡድናቸው ‘ታክቲካሊ’ ጥሩ እንደነበር ተናግረዋል።