ከክለብ ላይሰንሲንግ ጋር በተያያዘ ሰሞነኛ መነጋገርያ የሆኑት ሠራተኞቹ መጨረሻቸው ምን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል?
ለ2017 የውድድር ዘመን ጅማሬያቸው እንደከዚህ ቀደሙ የነበሩ ውስብስብ ችግሮቻቸው ተከትለዋቸው የመጡት ወልቂጤዎች አስገዳጁን የክለብ ላይሰንሲጉን መስፈርት ማሟላት ሳይችሉ በመቅረታቸው የሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታ በፎርፌ ለመሸነፍ ተገደዋል።
ትናንት በነበረው ዘገባችን የክለቡ የበላይ ኃላፊዎች አስፈላጊውን መስፈርት ለሟሟላት ክፍያዎችን ለመፈፀም እየተንቀሳቀሱ እንደነበረ እና ወደ ፌዴሬሽኑ ሁሉንም ነገር አሟልተው ካልመጡ በቀር ፍቃዱን ለማግኘት እንደሚቸገሩ ገልጸን ነበር። ዛሬ አመሻሽ ላይ የሳምንቱን ሁለተኛ ጨዋታቸውን ለማድረግ ቀጠሮ የተያዘላቸው ሠራተኞቹ ጨዋታውን ያደርጋሉ ወይስ ዛሬም በተመሳሳይ ፎርፌ በመስጠት ራሳቸውን ለከባድ የዲሲፕሊን ቅጣት ዳርገው ወደ ከፍተኛ ሊግ ይወርዳሉ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ሶከር ኢትዮጵያ ይህንን ዘገባ እስካጠናከረችበት ጊዜ ድረስ በወልቂጤ በኩል ክፍያውን ለመፈፀም ከሚደረግ ጥረት እና ተስፋ ውጭ ሙሉ ለሙሉ መስፈርቱን አሟልተው የሚጠበቅባቸውን ሰነድ በመያዝ ወደ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት አልደረሱም። ሰዓቶች እየገፉ በሄዱ ቁጥር የሚፈጠረውን ነገር አሁን መገመት ባይቻልም የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎች ካሉ የምንመለስበት ይሆናል።
ወልቂጤዎች የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ዛሬ ረቡዕ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ከንግድ ባንክ ጋር እንዲጫወቱ ቀጠሮ ተይዟል።